መጣጥፍ Articles

«ቲዎሎጂ ቢቀርስ»፡- እንዳለን «እንዳለ» እንቀበለው?

 

(ለእንዳለ በሽር የተሰጠ ምላሽ)

eraser_1347_1ሥነ መለኮትን መማር አልፈልግም ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ያ ማለት ግን ስለ እግዚአብሔር ምንም አታውቁም ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ስለ እግዚአብሔር በርከት ያለ የተሳሳተ ሐሳብ አላችሁ ማለት ነው፡፡
ሲ.ኤስ. ሉዊስ

በቅርቡ ወንድም እንዳለ በሽር ወንድም ማሙሻ ፈንታ በወንጌል ብርሐን ቤተ ክርስቲያን ላስተላላፈው እና በዩትዩብ በይነ መረብ ለተለቀቀው ጠንከር ያለ መልዕክት የሰጠውን ምላሽ አነበብኩ፡፡ ደነገጥኩም፡፡ ያስደነገጡኝ በወንድም ማሙሻ ላይ የሰነዘራቸው «ዘለፋዎች» አይደሉም፡፡ ያስደነገጠኝ «ፍቅር ነግሶ ቲዎሎጂ ቢቀርስ?» የሚለው አባባሉ ነው፡፡ የተሰማኝ ስሜት «ሰውየው የታወቀ አጭበርባሪ ቢሆንም ይወድሻል እና አግቢው!» ብሎ አንደሚመክር የጋብቻ አማካሪ ያለ ስሜት ነው፡፡ ምናልባት «ሥነ መለኮት ላይ የተመሰረተ ፍቅር ቢነግስስ?» አይነት ነገር ቢሆን ኖሮ ይህን ጽሁፍ ስጽፍ ባልተገኘሁም ነበረ፡፡ ግን ምን ያደርጋል ያ አልሆነም!
ወንድም እንዳለ ወንድም ማሙሻ በ«ጌታ ባሪያዎች» ላይ ሰነዘረው ላለው ትችት በሰጠው መልስ ላይ «ቲዎሎጂ ቢቀርስ…» በሚል በሥነ መለኮት ላይ የሰነዘራቸው ትችቶች ወንድም ማሙሻን ብቻ ሳይሆን እንደሱ የሥነ መለኮትን ጠበል የቀመሱትን ሁሉ የሚመለከት ነው ባይ ነኝ፡፡ እኔም በዚሁ ጉዳይ ላይ ትንሽ ለማለት ወደድኩ፡፡ የዚህ ጽሁፌ ዓላማ በወንድም ማሙሻ መልዕክት የተነሳ የተፈጠረውን ውዝግብ በቀጥታ የሚመለከት አይደለም፡፡ ይልቁንም ወንድም እንዳለ በበሰጠው ምላሽ ላይ የሥነ መለኮት ትምህርትን አስፈላጊነት በማኮሰስ ለሰነዘረው ትችት ምላሽ መስጠት ነው፡፡ በዚህችም አጭር ጽሁፍ ሥነ መለኮት ምንድን ነው? እንዴትስ ይጠናል? የሚለውን አነሳና ወንድም እንዳለ ስነ መለኮት ቢቀርስ ወደ ሚል ድምዳሜ ያደረሱትን የተበተኑ ሐሳቦች በማሰባሰብ ምላሽ በመስጠት ሥነ መለኮት ልናጠና እንደሚገባን ጥሪ በማቅረብ አጠቃልላለሁ፡፡
ሥነ መለኮት ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ይጠናል?
«ቲዎሎጂ ቢቀርስ» የሚል ድምዳሜ ላይ ሊያደርሰን ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ስለ ሥነ መለኮት ያለን መሠረታዊ ግንዛቤ የተዛባ መሆን ነው፡፡ ስለዚህ «ሥነ መለኮት ማለት ምን ማለት ነው?» ከሚለው ጥያቄ ብንጀምርስ? ሥነ መለኮት ማለት ስለ መለኮት ማሰብ ፣ ማመን እና መናገር ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ እያንዳንዱ በዚህች ምድር ላይ የሚኖር ሰው የራሱ ሥነ መለኮት አለው፡፡ ይህም ማለት እያንዳንዱ ሰው ስለ አምላክ ወይም አማልክት በአዎንታዊም ይሁን በአሉታዊ መልኩ ያስባል፡፡ አማኙ ስለ አምላክም ደግ፣ ርሁሩህ፣ አዛኝ፣ ጨካኝ ወ•ዘ•ተ እያለ በልቡ ያሰበውን በአፉ ይናገራል፡፡ የማያምነውም በተቃራኒ ስለ አምላክ አለመኖር ይናገራል፡፡ ይህ መረዳቱ ትክክለኛ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል፡፡ ጠሊቅ ወይም ግልብ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰውየውም የተቀባ ወይም መናፍቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው ሥነ መለኮታዊ ነው፡፡
ወደ ክርስትና ስነመጣ ሥነ መለኮት ማለት በቃሉ እና በልጁ በኩል ስለ ተገለጠው እግዚአብሔር ማሰብ፣ ማመን፣ መናገር ማለት ነው፡፡ እሱን ክርስቲያናዊ ሥነ መለኮት እንለዋለን፡፡ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሥነ መለኮታቸው በቤተ ሰባቸው ልማድ፣ በመጋቢያቸው ስብከት፣ ባነበቡት መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይሔም ሥነ መለኮት ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ ሥነ መለኮታቸው በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረተ፣ በአመክንዮ የተፈተሸ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄም ራሱን የቻለ ነው፡፡ በጥቅሉ የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ፣ ስለ እግዚአብሔር «የሆነ ነገር» የሚያምን ሰው የራሱ ሥነ መለኮት አለው፡፡ አንድ ክርስቲያን እኔም ምንም አይነት ሥነ መለኮት የለኝም ሊል አይችልም፡፡ እያንዳንዱ ሰው መሠረታዊ የሥነ መለኮት እውቀት አለው፡፡
ስለዚህ ትልቁ ጥያቄ ግለሰቡ እምነቱን በሚያጎለብት ሁኔታ በእግዚአብሔር ቃል እውነት ላይ ተመስርቶ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እና ልምምድን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መርምሮ እምነቱ ለማጎልበት ፍላጎት አለው ወይስ የለውም የሚለው ነው? «አዎን አለኝ፡፡ እንዴታ!» ከሆነ መልሱ፡፡ ይህን እውቀት የሚቀስምባቸው ሁለት መንገዶች አሉ፡፡ አንደኛው መደበኛ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት በመግባት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ ራስን ማስተማር ነው፡፡ «ጌታን ለመከተል ሥነ መለኮት ትምህርት ቤት መግባት ያስፈልጋል ወይ ብትሉኝ?» መልሴ በፍጹም ነው! መደበኛ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤትን ደጅ ያልረገጡ በቤተ ክርስቲያን ላይ ግን ታላላቅ ተጽዕኖ የፈጠሩ እማኞችን መጥቀስ እንችላለን ኤ. ደብሊው ቶዘር እና ዲ.ኤል. ሙዲን አለመጥቀስ ነውር ነው! እርግጠኛ ነኝ! የ«ሥነ መለኮት ሊቃውንትም» ቢሆኑ አንድ ሰው ሥነ መለኮት ትምህርት ቤት ካልገባ «ሊቅ» ሊሆን አይችልም የሚሉ አይመስለኝም! ካሉም ስለ ግብዝነታቸው እናመሰግናለን!
በጥቅሉ ክርስቲያን ውነ መለኮታዊ ፍጡር ነው፡፡ ይህን ስነ መለኮቱንም መደበኛ በሆነ እና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሊያገኘው ይችላል፡፡ የዚህ ምላሽ መሠረትም ይሄ ጽኑ እምነቴ ነው፡፡ እንዲያ ባይሆንማ ኖሮ ወንድሜ እንዳለ በመደበኛ ሁኔታ ሥነ መለኮትን ስላልተማረ ምላሽ መስጠት አይገባኝም ነበር፡፡
የወንድም አንዳለ ትችቶች
የወንድም እንዳለ ትችቶች በዋነኛነት ያነጣጠሩት በመደበኛው የሥነ መለኮት ትምህርት ውስጥ ባለፉ (በተለይ በ«ጌታ ባርያዎች» ላይ ትችትን በሚሰነዘሩ) አንዳንድ «የሥነ መለኮት ሊቃውንት» ላይ ነው፡፡ እስቲ እነዚህ ትችቶቾ ሚዛን የሚደፉ ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለውን እንመልከት፡፡
ሀ. ካርል ትሩማን «አያስፈልግም» ስላሉ ቢቀርብንስ!?
ወንድም እንዳለ የሚጠቀሳቸው ካርል ትሩማን የተሰኙ ሰው በዌስት ሚኒሰቴር ሴሚናሪ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መምህር እና የትምህርት ክፍሉ አካዳሚክ ዲን ታዋቂ ጸሐፊ ናቸው፡፡ እንዳለ የሥነ መለኮት ጥናት ለአማኙ ማህበረሰብ ፋይዳ አላመጣለትም ከማለታቸው የተነሳ የሐገራችንን ሁኔታ ፍንትው አድርገው ያሳያሉ ያለላቸው እኚህን የታሪክ አስተማሪ ነው፡፡ ዝርዝር መረጃውን እና ምንጩን ግን አልጠቀሰልንም፡፡
መጀመሪያ፣ ሰውየው ሥልጣናዊ በሆነ ሁኔታ መናገር ስለ ስነ መለኮት ጥቅም እና ጉዳት መናገር ይችላሉ ወይ? አይችሉም! የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መምህር ከመሆናቸው የተነሳ ከዚያ አንጻር ሊናገሩ ይችሉ ይሆናል፡፡ ሥነ መለኮትን በመደበኛ ሁኔታ ያላጠና ሰው ፤ ስለ ጥቁሙና ጉዳቱ ሊያብራራ ይችላል፡፡ ነገር ግን ተቀባይነቱ ስለተለያዩ መኪኖች ታሪክ የጻፈ ሰው ለጋራዥ ባለሙያ ስለ መኪና ጥገና የሚሰጠውን አስተያየት ያክል ነው፡፡
ሁለተኛ እኚህ ሰውስ እንዲህ ብለዋል ወይ የሚለውን ማንሳቱ ተገቢ ነው? በእኚህ ሰው ጽሁፍ ላይ ባደረግኩት ዝርዝር ምርመራ ወንድማችን ያለው ነገር « በድንግዝግዝ የተወሰደው» በዌስት ሚኒስቴር ጆርናል ላይ በታተመው እና የመምህርነት ሥራቸውን በጀመሩ ጊዜ የሰጡት የመጀመሪያ ገለጻቸው ላይ ነው፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት “ድነት በአንድ ሰው ጥልቅ ሥነ መለኮታዊ ግንዛቤ ላይ ወይም ደግሞ ውስብስብ የሆኑ ሥነ መለኮታዊ ጽንሰ ሐሳቦችን በጥልቀት በመረዳቱ ላይ የተመሰረተ አይደለም” ይሄ ምን ስህተት አለው! ለዚህም ነው ለድነት የሚያፈልጉን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶች ቁልጭ ብለው የተቀመጡልን፡፡ ትሩማን ግን እዚህ ላይ አያበቁም በዚያው አፋቸው እንዲህ ይላሉ፡- «…የአሥተምህሮ ጥልቀት የሌለው ክርስትና ቤተ ክርስቲያንን ለማቆም ሆነ የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት ለረጅም ዘመናት ለማስቀጠሉ ዋስትና የለውም፡፡ ይህም ማለት ለቅዱሳን አንድ ጊዜ የተሰጠውን እምነት ከትውልድ ወደ ትውልድ፣ ከቦታ ወደ ቦታ ሊያሸጋግር አይችልም ማለት ነው፡፡» ታዲያ እኚህ ሰው ናቸው ሥነ መለኮት ለአማኞች ምንም ፋይዳ የሌለው ለመሆኑ ማስረጃ ተብለው ሊቀርቡ የሚገባቸው? በእርግጥ ትሩማን ላይ ትችት ያስነሳባቸው ነገር የሥነ መለኮት ሊቃውንቱን ክርስትናን «እውቀት ተኮር ብቻ» አደረጋችሁት ማለታቸው ነው፡፡ ይሄ ግን በምንም አይነት መንገድ ሥነ መለኮቱ ቢቀርስ ወደ ሚል መረዳት አላደረሳቸውም፡፡ እሱ ሊጠቅሰው በሞከረው ጽሁፍ ውስጥም እሱ ያቀረበውን ሐሳብ የሚደግፍ ነገር አላገኘሁም፡፡ (በኢሜይል ለምትጠይቁኝ ሁሉ ጽሁፉን እልካለሁ!) የሰውየውን ተጨማሪ ጽሁፎች ሳገላብጥም የወንድሜን ሐሣብ የሚደግፍ አንዳች ነገር አላገኘሁም፡፡
በሦስተኛ ደረጃ እሳቸው ራሳቸው ብለውት ቢሆንስ፣ እሳቸውም ሳይሆኑ በሥነ መለኮት ሊቅ የሆነ ሰው ብሎትስ ቢሆን እሱ በማለቱ ብቻ ሥነ መለኮት ይቅር ልንል እንችላለን? እንዴት ሆኖ! ለዚህ ድምዳሜ የቀረበውን ማስረጃ በእግዚአብሐየር ቃል እውነት እና በንጹህ ምክንያታዊ ፍታሣ ካለጤነው ድምዳሜ ላይ ልንደርስ አንችልም፡፡ እንዲያ ካሰብን እኮ ታዋቂ ሰው ያለውን በማስተጋባት (Appeal to Authority) የአመክንዮ ሕግን ተላልፈናል ማለት ነው፡፡
ይሄ ምክንያት እንዴት የሐገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ፍነትው አድርጎ እንደሚያሳይ አልገባኝም፡፡ የሥነ መለኮት ትምህርት ተማሪዎች በአማኙ ሕይወት ውስጥ ረብ አላመጡም ከሆነ ሕዝቡን ከበላተኛ እየታደጉ ያሉትን በመድረክም ሆነ በጽሁፍ ብርቱ የሆኑ ወዳጅ – አስተማሪዎቻች፣ አስተማሪ- ወዳጆቻችንን ፣ወዳጅ- ተማሪዎቻችንን፣ ተማሪ-ወዳጆቻችን አንድ ሁለት መቁጠር እንችላለን፡፡ (እስቲ ሥነ መለኮት ተምራቸሁ፣ አስተምራችሁ ሕይወታችሁ የተለወጠ እጃችሁን አውጡ!!)
ለ. ያረጀ ያፈጀ ስነ መለኮት ስለሆነ ቢቀርብንስ!?
እውነት ነው! ለፈተና የተጠና ሥነ መለኮት የሚያስተምሩ በርካታ ግለሰቦች አሉ! እኔም ብሆን አንዳንድ ጊዜ ከቤተ እምነታቸው በስተቀር ቁርጥ ግሩደምን የሚመስሉኝ ሰዎች አሉ፡፡ እርግጥ ነው የአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ወይም ደግሞ ከአራት መቶ ዓመት በፊት የነበረን ሥነ መለኮት የሚያቀነቅኑ ሰዎችም እንዲሁ አሉ፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ የቤተ እምነታቸው መሥራች የሆነውን ግለሰብ አበክረው የሚጠቅሱ የዋሃን አሉ፡፡ (እኔም ራሴን «ጆን ዌዝሊ» እንደማበዛ አውቄያለሁ!) አንዳንዶቻችን እኮ ከጢም አቆራረጣቸው ጀምሮ እነ ሉዊስ ሻፈርን ለመቅዳት ሞክረናል፡፡
እንዲያው ለመሆኑ የሆነስ ሆነና እውነት በዕድሜ መለካት የጀመረችው መቼ ነው፡፡ የድሮ ነገር ሁሉ መጥፎ ነው ያለው ማን ነው? በዘመን ከሄድንማ መሠረታዊ የአዲስ ኪዳን አሥተምህሮዎች እኮ ሁለት ሺኅ ዓመታት ያለፈባቸው ናቸው፡፡ የብሉይ ኪዳንም አይነሳ! ለመሆኑ መጤ የሆነ ነገሮች ሁሉ ልክ ናቸው ያለውስ ማን ነው? የአንድ ነገርን እውነትነት የምንለካው በጊዜ ርዝመት ነው ሆነ እንዴ? እንዲያው ያረጀ ያፈጀ ሥነ መለኮት የሚማሩ የሚያስተምሩ ስላሉስ ሥነ መለኮት ቢቀርብ ማለት እንችላለን?
ታዋቂው ጸሐፊ ሲ ኤስ ሉዊስ አንድ እውነት «አሮጌ» ስለ ሆነ ውሸት «አዲስ» ስለ ሆነ እውነት ሊሆን እንደማይችል ደጋግሞ በመናገር ይታወቃል፡፡ እውነት አንደ ፋሽን የሚለዋወጥ አይደለም፡፡ ሲ ኤስ ሊዊስ ይህንን አይነቱን አመለካከት የቅደም ተከተል ልክፍት(Chronological Snobbery) ይለዋል፡፡ አንዳንዶቻችን የእነ ኤጲስ ቆጶስ ቀለሜንጦስ ሐተታዎች ልባችንን ሲያሞቁት፣ ሌሎች ደግሞ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፉ መጽሐፍት የመስጧቸዋል፡፡ አንዳንዶቻችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እንድምታ ሲያስደምመን፣ ሌሎች ደግሞ የ2014 መጽሐፍት የሚያነቡ እና ሐገር በቀል እና ዓለም አቀፉን ሥነ መለኮት ያስተነትናሉ፡፡ ሁላችንም ግን እነዚህ ነገሮች ሁሉ እንደ ደራሲው በዘመናት መካከል በሸመገለው መጽሐፍ ፊት አሮጌም አዲስም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የያዙት እውነት ከቃሉ ጋር ከሰመረ መቼም ይጸፍ መቼ ሰርክ አዲስ ናቸው ፤ ከቃሉ ጋር ከተጣረሱ ግን መቼም ይጻፉ መቼ ፋሥን ያለፈባቸው ናቸው፡፡
ታዲያ ይሄስ ሥነ መለኮት ቢቀርብን ያሰኝ ይሆን?
ሐ. ያልተማሩ ሰዎች ስለ ተቀቡ ቢቀርብንስ!?
እንኳን «ተቀቡ!» እና ታዲያ ምን ይጠበስ? ይህ ጉዳይ አዲስ ነገር መሆኑ ነው እንዴ? መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እኮ ሐዋርያት ራሳቸው «ያልተማሩ» ተብለዋል፡፡ በጸሐፍት ፣ በፈሪሳውያን እና በካህናት አለቆች ዘንድ ሲታዬ ያልተማሩ ነበሩ፡፡ ነገር ግን እነሱን ያለመማር መለኪያ ልናደርጋቸው አንችልም ምክንያቱም እነሱ በቀጥታ ከጌታ ከራሱ የሥነ መለኮትን ትምህርት የቀሰሙ ሰዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የቀባቸው ባለመማራቸው አዝኖ ሳይሆን ስለ ተማሩ ነበር፡፡ ታዲያ ያልተማሩ ሰዎች መቀባት አለመማርን ለመቀባት መንስዔ ያደርገዋል እንዴ? በየት በየት ወዳጄ ! ይሄ ማለት እኮ በአንድ መንደር የባህል ሐኪሞች ስለ በዙ የህክምና ትምህርት አያስፈልግም እንደ ማለት ነው፡፡ የባህል ሐኪሞች እንኳን ዘመናዊ ትምህርት ያስፈልገናል እያሉ ነው፡፡ ወንድም እንዳለ ለዚህ ጉዳይ በሚሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ ላይ፡-
«ሥነ መለኮት ሳያጠኑ በዚህ ዘመን በትንቢት ጸጋ የተቀቡ የጌታ ባርያዎች መኖራቸው እርግጥ ነው ፡፡ እነዚህ ሰዎች የስነ መለኮት ደጃፍ አልረገጡም፡፡ … ስነ መለኮት ደጃፍ ስላልረገጡ የሚወቅሳቸው የለም ፡፡ ዳሩ ግን በምድረ በዳ ልክ እንደ ጌታ ደቀ መዛሙርት ከጌታ እግር ስር ቁጭ ብለው የክስትናን መልክ በተሞክሮ አጥንተዋል፡፡»
ወንድሜ ሊያጠኑ ይችላሉ! የትኛውም ሰው አጥንቻለሁ ማለት መብቱ ይመስለኛል፡፡ ትልቁ ጥያቄ ግን ያጠኑት በትምህርት በሕይወታቸው እየኖሩት ነው ወይ የሚለው ነው? ኖረው ከሆነ ጥሩ ነው! የማይኖሩ እና ከእግዚአብሔር ቃልጋር የማይጣጣሙ ከሆነ ግን «የጌታ ባርያ»፣ «የተቀባ ነብይ»፣ «ሜጀር ፕሮፌት»፣ «ዶ/ር»፣ «የሥነ መለኮት ሊቃውንት» በሚሉ መጠሪያዎች ብንሸሽጋቸውም መገለጣቸው አይቀርም፡፡ ለሚነሳባቸው ሥነ መለኮታዊ ጥያቄም ሆነ አስተያየት ምላሻቸው «ጌታ በቀባው ላይ አፍህ አታላቅ»፣ ለምን ተነካሁ ከሆነ ሥነ መለኮት ቢማሩ ያቀናቸዋል እንጂ አይሰብራቸውም፡፡
በዚህ ከተስማማን የምናትተው ነገር ከሕይወታችን ጋር ተጣጥሞ ካልታየ «በጌታ እግር ስር ቁጭ ብዬ ተምሬያለሁ» ማለት በራሱ ሥነ መለኮት ላለመማር ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡

መ. ሥነ መለኮት ሰዎችን በወንጌል (በፈውስ) ለመድረስ ስለማይጠቅም ቢቀርብንስ!?
አማኞች በክርስቶስ አካል ውስጥ ሰዎች የተሰጣቸው ጸጋ ልዩ ልዩ ነው፡፡ አንዳንዶች አስተማሪዎች ፣ አንዳንዶች ወንጌላውያን፣ አንዳንዶች እረኞች ወ.ዘተ ናቸው፡፡ ታዲያ በየት ሀገር ነው አስተማሪዎችን ለምን በፈውስ አላገላገላችሁም፡፡ እረኞችን ደግሞ ለምን ትንቢት አልተናገራችሁም ብለን የምንከሰው፡፡ የአንዱን ጸጋ መለኪያ ለሌላው የምናውለው!?
አንድ የሥነ መለኮት ተማሪ ሥነ መለኮት መማሩን መለካት የምንችለው እግዚአብሔር ከሰጠው ጸጋ አንጻር እንጂ ለሌላው ሰው በተሰጠ ጸጋ ሊሆን አይገባም፡፡ አንድ የሥነ መለኮት ተማሪ «የትንቢት ስጦታ» ኖሮት ሥነ መለኮት ተምሮ በትንቢት ስጦታው ማገልገል ካልቻለ ጥያቄ ልናነሳ እንችል ይሆናል፡፡ ወንጌል መመስከር የእያንዳንዱ አማኝ ሃለፊነት ቢሆንም ወንጌላዊውንም በተመሳሳይ መስፈርት ልንዳኘው አንችልም፡፡ ነገር ግን ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋት ወንጌልን መመስከር ብቻ ሳይሆን አማኞች ደቀ መዛሙርት ማድረግ ጭምር ነው፡፡ ደቀ መዛሙርት ማፍራት የእያንዳንዱ አማኝ ሃላፊነት ቢሆንም ደቀ መዛሙርትን በማፍራት ሂደት ውስጥ እየተሳተፈ ያለን አስተማሪ («የሥነ መለኮት ሊቅ») ወንጌል ሰብከህ ብዙሃን ጌታን አልተቀበሉም ብለን የወንጌላዊውን ያህል ልንጨቀጭቀው አይገባም፡፡ ለዚያ አይደል የክርስቶስ አካል እንጂ የክርስቶስ አይን ወይም የክርስቶስ መዳፍ ያልተባልነው! ለዚህ አይደል አብረን መሥራት የማንነታችን መገለጫ የሆነው፡፡
የሥነ መለኮት ዋነኛ ዓላማ ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ንዲያድጉ እና ምስክሮች እንዲሆኑ ቢሆን ዋነኛ ዓላማው ሰዎች ጸጋቸው ምንም ይሁን ምን ሰዎች ስለ የሚያስቡትን ፣ የሚያምኑትን እና የሚያደርጉት ነገር ከእግዚአብሔር ቃል አንጻር እንዲያደርጉ ማስተማር ነው፡፡ ስነ መለኮታዊ ትምህርትን ልንለካበት የሚገባው መሥፈርት አንድን ሰው ከእገዚአብየር የተማረ፣ ስለ እግዚእበሔር የተማረ እና ወደ እግዚብሔር የሚመራ ነወይ የሚለው ነው፡፡ በአጭሩ የትክክለኛ ሥነ መለኮት መለኪያው «አማኞች እግዚአብሔርን(ቃሉን) ያማከለ አስተሳሰብ ፣ እምነት እና ሕይወት እንዲኖራቸው አግዟል ወይ?» የሚለው ነው፡፡
ሠ. ሥነ መለኮት «የጭንቅላት ጨዋታ» እንጂ የመንፈስ ቅዱስ የልብ ትርታ ስላልሆነ ቢቀርብንስ!?
ይሄ ነገር በተደጋጋሚ የምሰማው ነገር ነው፡፡ እርግጥ ነው ሥነ መለኮት «የጭንቅላት ጨዋታ» የሚመስላቸው በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ እንደዚያ የሚያደርጉትም ይኖራሉ፡፡ አንዳንዶች «የሥነ መለኮት ሊቃውንት» ሲጸልዩ የእውነት የማይመስላቸው ሰዎች አይቻለሁ፡፡ ለእነዚህ ሰዎች እርግጥ ነው ሥነ መለኮት «የጭንቅላት ጨዋታ» ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን የእኛ ልምምድ እውነታውን አይለውጠውም፡፡ ታላላቅ የሥነ መለኮት መመሪያ መጽሐፍቶቻችን እንኳን ብንቃኝ የሥነ መለኮት ጥናት መጀመሪያ ጸሎት እንደ ሆነ አበክረው ይናገራሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በዓለም ላይ የምናውቃቸው ታላላቅ የሥነ መለኮት ምሁራን ማርቲን ሉተር፣ ጆን ካልቪን፣ ጆን ዌዝሊ፣ጄ አይ ፓከር፣ ጆን ፓይፐር ፣ ኤን ቲ ራይት ወ.ዘ.ተ ጸሎት እና የእግዚአብሔርን መንፈስ የልብ ትርታ ማድመጥ ዋነኛ ጉዳይ እንደ ሆነ ይናገራሉ፡፡ አገራችንም ውስጥ ባሉ በርከት ያሉ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተመሳሳይ ትኩረት ሲሰጠው አስተውያለሁ፡፡ እንዲያውም በሕይወቴ ከማውቃቸው የተቀቡ ሰዎች መካከል በርካቶቹን ያገኘኋቸው ሥነ መለኮት ትምህርት ቤት ነው ብል አጋንን ይሆን?
ስለዚህ ጥቂት ደረቅ ያሉ እና ሥነ መለኮትን የጭንቅላት ጨዋታ የሚያደርጉ ሰዎች በማየት ብቻ ሥነ መለኮት ቢቀርስ ማለት ጨጓራ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ስላሉ መመገብ እናቁም ማለት ነው? ይሄን ደግሞ መሞከር ነው?
ማጠቃለያ
ወንድማችን እንዳለ ሥነ መለኮቱ ቢቀርብስ ወደሚል ድምዳሜ እንዲደርስ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አብዛኞቹ የመነጩት ከሥነ መለኮት ትምህርት ቤቶቻችን «ባዕድ» መሆን እደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ ብዙዎቹ የሥነ መለኮት መምህራን ከቤተ ክስቲያን ጋር ያላቸው የአይጥና የድመት አይነት ግንኙነት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ሳይሆን እነሱ የትችት አቅማቸውን የሚፈትሹባት የቤተ ሙከራ አይጥ ናት፡፡ ሁሉም ግን እንዲህ አንዳለሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ግን ሥነ መለኮትን አካዳሚያዊ ብቻ ስለሆነ ቢቀርብንስ ወደሚል ድምዳሜ አያደርሰንም፡፡ ሥነ መለኮትን በመደበኛ ትምህርት ቤት ውስጥ ገብተን መማር የሚገባን መደበኛ ካለሆነ የሥነ መለኮት ጥናት ዕውቀት ማግኘት ስለማንችል ሳይሆን እምነታችንን አጎልምሰን ይበልጥ ጌታን ለማገልገል ነው፡፡ አገርን ለመጠበቅ «ከሚሊሻ ይልቅ መደበኛ ሠራዊት ያፈለግን ለምንድን ነው?» ብለን ብንጠይቅ ምላሹን በቀላሉ ማግኘት እንችላለን፡፡
የካርል ትሩማን አያስፈልግም ስላለ መማር የለብም፡፡ ያረጀ ያፈጀ ስነ መለኮት ስለሆነ መማር የለብንም፡፡ ያለተማሩ ሰዎች ስለተቀቡ መማር የለብንም፡፡ ስነ መለኮት ሰዎችን በወንጌል (በፈውስ) ለመድረስ ስለማይጠቅም መማር የለብንም፡፡መንፈስ ቅዱስ የጭንቅላት ጨዋታ እንጂ የመንፈስ ቅዱስ የልብ ትታ ስላልሆነ መማር አያስፈልግም፡፡ በማለት ወንድማችን እንዳለ በጽሁፉ ውስጥ ያስቀመጣቸው ነገሮች ስሜታዊነት እንጂ አመክንዮአዊነት የማየታይባቸው ናቸው፡፡ የዚህ ነገር ምንጭ ለሥነ መለኮት መምህራን ትችት ካለን ጥላቻ የመነጨ ወይም ደግሞ ስነ መለኮት ማጥናት ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ካለመገንዘብ የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡ ደጋግማ ብትሞክር ስላልደረሰችበት ይሄ እነጆሪ መራር ነው እደለችው ቀበሮ አንድን ሐሳብ ፊት ለፊት ለመሞገት ጉልበት ስናጣ በጥቅሉ ማጠልሸት ብዙ ፋይዳ የለውም፡፡ በመደበኛ ስነ መለኮት ትምህት ቤት ገብተን በመማርም ሆነ መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ በግላችን ስነ መለኮትን በማጥናት አግዚአብሔርን ማገልገላችንን እንቀጥል፡፡

Advertisements

ምን ሐሳብ አለዎት?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s