Uncategorized

ፐርፕቱዋ ፡- ሞትን የገደለች አራስ

ነጻ ትርጉም በአብነት አባቡ

perptuaከክርስቶስ ልደት በኋላ በ202 ልዑል ስፕቲሚየስ ሰርቨስ ሰዎች ክርስትናን እንዳይቀበሉ በይፋ አገደ፡፡ ይህ ዐዋጅ ከወጣ አፍታም ሳይቆይ በሰሜናዊ አፍሪካ በዛሬዋ ቱኒዚያ ጭካኔ የተመላበት ስደት ተነሳ፡፡ በዚህ ተመሳሳይ ወቅት በካርቴጅ ከተማ ፐርፕቱዋ የተሰኘች ወጣት ክርስትናን ተቀብላ ለጥምቀት እየተዘጋጀች ነበር፡፡ ፕርፕቱዋ፣ ምንም እንኳን ይህ ዓለም ከተቀላቀለ ጥቂት ጊዜ የሆነው ጨቅላ የምታጠባ ወገቧ ያልጠና አራስ እና የ22 ዓመት ወጣት ብትሆንም ተይዛ እስር ቤት ከመወርወር ግን አላመለጠችም፡፡ ከእስር በኋላ ያለውን ከምተርክላችሁ ታሪኩን ከሷው አንደበት ስሙት፡-

እስር ቤት ከገባሁ በኋላ አባቴ ለእኔ ካለው ፍቅር የተነሳ ይሄንን ክርስትና የተባለ ነገር እርግፍ አድርጌ እንድተው አጥብቆ ይጎተጉተኝ ጀመር፡፡ አኔም ንዝንዙ ሲበዛብኝ «አባዬ አልት እዛ ፊት ለፊታችን ያለውን የውሃ መያዣ ማሰሮ ታየዋለህ?»

«አዎ» ሲል መለሰ፡፡

«ታደያ ለዚያ ማሰሮ ከማሰሮ ውጪ ሌላ መጠሪያ ሊሰጠው ይችላል?»

«እንዴት ሆኖ ልጄ» አለኝ አይን አይኔን በጉጉት እያየ፡፡

«አባይዬ እኔም ልክ እንደዚያው ክርስቲያን ተብሎ ከመጠራት ውጪ ሌላ መጠሪያ የለኝም፡፡» አልኩት ፈርጠም ብዬ፡፡

አባቴ «ክርስቲያን» የሚለው ቆሻሻ ቃል ከእኔ አንደበት ሲወጣ በመስማቱ ቱግ አለ፡፡ ፊቱ ጠቀርሻ መሰለ፡፡ ከመቀመጫው ተነስቶ በመጠየፍ እያየኝ ተጠጋኝ፡፡ አይኔን ጎልጉሎ ሊያወጣው ምንም አልቀረውም፡፡ ንዴቱን እንደ ምንም ተቆጣጥሮ ወደ ጉዳዩን ሄደ፡፡ ከዚያን በኋላ ሰይጣን ሰራሽ ጭቅጭቁን ይዞ የውሃ ሽታ ሆነ፡፡

ጠርጥዮስ እና ፖምፖኒየስ የተባሉት የተባረኩ ወንድሞች ወታደሮቹ አግባብተው ከማጎሪያው ወጥተን ወደ ተሻለ እስር ቤት እንድንዛወር አደረጉ፡፡ ለጥቂት ሠዓታትም ቢሆን ዘና አልን፡፡ ከረሃብ የተነሳ ሊሞት የተቃረበውን ጨቅላ ልጄን አጠባሁ፡፡ እናቴን ሳያት ከጭንቀቴ የተነሳ ስለ ልጁ ብዙ የማላስታውሰውን ነገር ቀበጣጠርኩ፡፡ ወንድሜንም ግን ላጽናናው ሞከርኩ፡፡ ልጄንም እንዲንከባከቡልኝ አደራ አልኳቸው፡፡ ለእኔ በማዘን ሐዘን ሲለበልባቸው በማየቴ አጥንት የሚሰረስር ህመም ተሰማኝ፡፡ እነሱን ይህንን አይነት ስሜት ሲፈራረቅብኝ በርካታ ቀናት አለፉ፡፡ በመጨረሻም ልጄ ከእኔ ጋር በእስር ቤት እንዲቆይ ፍቃድ አገኘሁ፡፡ ልጄን በማግኘቴ እና ጭንቀቴም በመቃለሉ ጤናዬ ተመለሰ፡፡ በድንገትም እስር ቤቱ ቤተ መንግሥት የሆነ መሰለኝ፡፡ ከዚህም የተነሳ ከእስር ቤት የመውጣት ፍላጎቴ ሁሉ ጠፋ፡፡

የፐርፕቱዋ ሕልም

ከቀናት በኋላም ወንድሜ «እህት ዓለም አንቺ በጣም ዕድለኛ ሴት ነሽ! እስቲ እባክሽ ምን እደሚደርስብሽ ጌታን ለምን አትጠይቂውም?» አለኝ፡፡

ከማያልቀው በረከቱ ነፍሴን ያረካትን ጌታዬ ማነጋገር እደምችል ስለማወቅ ለውንድሜ እንደምጠይቀው ቃል ገባሁለት፡፡ ወዲያውኑ ጥያቄዬን አቀርብኩ፡፡ ጌታም የሚከተለውን ነገር በሕልሜ አሳየኝ፡፡

በሕልሜም ወደ ሰማይ የተዘረጋ የመዳብ መሰላል አየሁ፡፡መሰላሉ ግን በጣም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ በከፍተኛ ጥረት ወደ ላይ ሊወጣበት የሚችለው አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ እዚህ መሰላል ላይ ከብረት የተሰሩ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ሰይፍ፣ጦር ፣ መንጠቆ፣ ጩቤ እና ወረንጦ ተበይደውበታል፡፡ ከዚህም የተነሳ በጥንቃቄ በመሰላሉ ላይ የማይወጣ ተንሸራቶ ይወድቅና አካሉ በእነዛ መሳሪያዎች ሲተለተል አይ ነበር፡፡

ከመሰላሉ ሥር ደግሞ ግዙፍ ዘንዶ ነበር፡፡ ዘንዶው መሰላሉ ላይ ለመውጣት የሚፍጨረጨሩትን ሰዎች ይተናኮላቸውና እንዳይወጡም ያስፈራራቸው ነበር፡፡ ከእነሱ መካከል በገዛ ፍቃዱ መሰላሉ ላይ የወጣው ሳታውረስ(የፐርፕቱዋ የደቀ መዝሙርነት መምህር) ነበር፡፡ ምንም እንኳን መጀመሪያ በታሰርን ጊዜ ባይኖርም ፣ በኋላ ግን ታላቅ ብርታትን ሰጥቶን ነበር፡፡ ሳታወረስ መሰላሉ ጫፍ ላይ ሲደርስ ፊቱን ወደ እኔ መልሶ «ፕርፐቱዋ…እጠብቅሻለሁ፡፡ ዘንዶው አንዳይነክስሽ ተጠንቀቂ!» አለኝ፡፡

እኔም «በክርስቶስ ኢየሱስ ስም አይነክሰኝም!» አልኩት፡፡

ዘንዶውም እኔን የፈራ በሚመስል ሁኔታ ከመሰላሉ ሥር አንገቱን ብቅ አደረገ፡፡ እኔም አናቱን እንደ መጀመሪያ ደረጃ በመጠቀም ወደ ላይ ወጣሁ፡፡

መሰሰላሉን ወጥቼ ከጨረስኩ በኋላ ሰፊ የአትክልት ስፍራ አየሁ፡፡ በዚያም ስፍራ የእረኛ ልብስ የለበሰ ጸጉሩ የሸበተ ረጅም ሰውዬ ተቀምጦ ወተት እያለበ ነበር፡፡ በሺ የሚቆጠሩ ነጭ ልብስ የለበሱ ሰዎችም ከበውት ተቀምጠው ነበር፡፡ ከተጎነበስበት ቀና ብሎ ትኩር ብሎ አየኝና ፈገግ ብሎ «ስለመጣሽ ደስ ብሎኛል ልጄ!» አለኝ፡፡

ጠራኝ እና ከሚያልበው ወተት ላይ አንድ ጉንጭ የሚሆን እጄ መዳፍ ላይ አፈሰሰልኝ፡፡ ትኩር ብዬ አየሁት እና ግጥም አድርጌ ጠጣሁት፡፡ በዙሪያው የቆሙትም ሰዎች በአንድ ድምጽ «አሜን» አሉ፡፡ ከዚህም ድምጽ የተነሳ ከእንቅልፌ ባነንኩ፡፡ የወተቱ ጣዕም ግን አፌ ውስጥ ነበር፡፡

ይህንን ሕልሜን ለወንድሜ ስነግረው ተስፋ ቆረጠ፡፡ በማጎሪያው ውስጥ የምንገኝ ክርስቲያኖች ምንም ተስፋ እንደሌለን አወቅን፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላ ለፍርድ እንደምንቀርብ ጭምጭምታ ተሰማ፡፡ አባቴም በጭንቀት ጉስቁልቁል ብሎ አሳምናታለሁ የሚልን ተስፋ አርግዞ መጣ፡፡

«ልጄ» አለኝ «እባከሽ ስለ ሽበቴ ስትይ ለእኔ ለአባትሽ እዘኚልኝ፤ አባትሽ ተብዬ መጠራት የሚገባኝ ከሆነ ፤ ከወንድሞችሽ አብልጬ ወድጄ፣ እዚህ እድሜሽ እስክትደርሽ ተንከባክቤሽ አሳድጌሽ ከሆነ እዘኚልኝ፡፡ የሰው መዘባበቻ እንድሆን ጥለሽኝ አትሂጂ፡፡ ስለ ወንድሞችሽ፣ ስለ እናትሽ፣ ስለ አክስትሽ አስቢ፡፡ እሱ ይቅር ስለዚህ ጡት ስላልጣለ ልጅሽ አስቢ አንቺ ከሞትሽ ማን ይንከባከበዋል?…እባክሽ የእኔ ልጅ ትዕቢትሽን ተይ! ሁላችንንም ተስፈጂናለሽ! በአንቺ የተነሳ ሁላችንም እናልቃለን? ተይ ልጄ?»

አባቴ እጄን እያሳመ እግሬ ላይ እየወደቀ እየተነሳ በፍቅር ይህንን ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ ያጽናናዋል ብዬ ያሰብኩትን ነገር ተናገርኩ፡፡ « አባይዬ በማጎሪያው ውስጥ የሚሆነው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ነው፡፡ በእስረኞቹ መታጎሪያ ውስጥ እግዚአብሔር የፈቀደው ነገር ይሆናል፡፡ አባዬ ጌታ እኮ ለራሳችን ፍቃድ አልተወንም፡፡ ሁላችንንም በእሱ ፍቃድ ስር ያለን ሰዎች ነን፡፡ እህ …አባዬ;»

ምንም መልስ ሳይሰጠኝ እያዘነ ጥሎኝ ሄደ፡፡

አንድ ቀን ቁርስ እየተመገብን ሳለ በፍጥነት ተወሰድን ( በአገረ ገዢው በሂላሪያነስ) ፊት ቀረብን፡፡ ሌሎቹ በሙሉ ሲጠየቁ ጥፋተኝነታቸውን አመኑ፡፡ የእኔ ተራ በደረሰ ጊዜ አባዬ ጨቅላ ልጄን ይዞ ከተፍ አለ፡፡ አግሬን እየጎተትኩ ስጓዝ ወደ ሕዝቡ ጎትቶ «የኔ ልጅ እባክሽ … ልጄ …ለልጅሽ ስትይ እንኳን ይህን መስዋዕት አቅርቢ አለኝ፡

ሐገሪ ገዢው ሂላሪያነስ «ላዛውነቱ አባትሽ እዘኚለት ፡፡ ለእሱ እንኳን ቢቀር ለዚህ ጨቅላ ህጻን እዘኚ፡፡ ቶሎ በይና ለቄሳር ጤና መስዋዕቱን አቅርቢ!» አለኝ ጅብራ መስሎ ወደ ተገተረው የቄሳር ሐውልት በአገጩ እየጠቆመ፡፡

«አላድርገውም…በፍጹም አላደርገውም!» ስል ተቃወምኩ፡፡

ሂላሪያነስም «ክርስቲያን ነሽ?» ብሎ ጠየቀኝ

«አዎ ነኝ» አልኩት ፡፡

አባቴ እኔን ለማግባባት ደጋግሞ ሲሞክር ያየው ሂላሪያነስ መሬት ላይ ጥለው በዱላ አንዲደበድቡት አዘዘ፡፡ እኔ ራሴ የተመታሁ ያክል በአባቴ ያለፈው ዱላ ነዘረኝ፡፡ ለአባቴ ዱላው እኔ ላይ ያረፈ ያህል አዘንኩለት፡፡ በመቀጠልም ሂላሪያነስ በሁላችንም ላይ ፍርድ ሰጠ፡- በስቴዲየም በተሰበሰበ ሕዝብ ፊት ለተራቡ አውሬዎች እንድንሰጥ ተፈረደብን፡፡ ይህንን ስሰማ ሁላችም በከፍተኛ ደስታ ወደ እስር ቤት ተመለስን፡፡

በአምፊ ቲያትሩ ውስጥ

[ፐርፕቱዋ ታሪኩን ከዚህ በላይ መቀጠል አልታደለችም፡፡ በአምፊ ቲያትሩ ውስጥ የሆነውን ነገር ያየ የአይን ምሥክር ማርች 7 ፣203 የተከሰተውን ነገር እንዲህ ተርኮታል፡፡]

በሞታቸው ሞትን ድል የሚሱበት ቀን ሲነጋጋ በታላቅ ደስታ ተሞለተው፣ ከፍርሃት ይለቅ በደስታ ሰክረው ወደ ገነት እንደሚጓዝ ሰው ወደ አምፊ ቲያትሩ ተወሰዱ፡፡ በጌታ የተወደደችው ፣ የክርስቶስ ሙሽራ ፐርፕቱዋ ፊቷ በደስታ እያብርቀረቅ በተረጋጋ ሁኔታ አፍጥጦ ይመለከታቸው የነበረው ሰው በላ ሕዝብ በሐፍረት እንዲያቀርቅር እያደረገች ገባች…

ስቴድየሙ የውስጥ በር ላይ ሲደርሱ ወንዶቹ የሳተርንን ካህናት ልብስ ሴቶቹ ደግሞ የሴሬስን ሴት ካህናት ልብስ በግድ አለበሷቸው፡ ፕርፕቱዋ ግን አልለብስም ብላ ተቃወመች፡፡

“ወደዚህ የመጣነው በፍቃዳችን ነው፡፡ በመሆኑም ነጻነታችን ሊገፈፍ አይገባም፡፡ እንዲህ አይነት ጌታን የሚያዝን ተግባር ላለመፈጸም በሕይወታችን ተወራርደናል፡፡ እናንተም ይህንን ላለማድረግ ተስማምታችኋል፡፡

ለካ ፍትህን የማያውቁ ሰዎችም ፍትህን ያውቃሉ፡፡ ወታደራዊው ምክር ቤት በፐርፕቱዋ ሐሳብ ተስማማ፡፡ ሌሎቹም ልብሳቸው ተቀይሮላቸው ወደ ስቴዲየም እንዲገቡ ተደረገ፡፡ የዘንዶውን አናት እየረገጠች መሆኑን ያወቀችው ፐርፕቱዋ መዘመር ጀመረች፡፡ በቁጣ የገነፈለው ሕዝብ ሊቦጫጭቃቸው ሲነሳ የሐገረ ገዢው ጠባቂዎች አስቆሙት፡፡ ሂላሪያነስ ፊት ለፊት ሲቆሙም በአንቅስቃሴያቸው እና በፊታቸው ገጽታቸው አንተ እንደፈረድክብን እግዚአብሔር ይፍርድብሃል የሚሉ ይመስሉ ነበር፡፡

ሞትን እንደትንኝ በሚያዩት በእነዚህ ሰማዕታት የተቆጣው ሕዝብ የሰማይ ስባሪ በሚያካክሉት ግላዲያተሮች እንዲደበደቡ ጠየቀ፡፡ እነሱም ግን በሕዝቡ ጥያቄ ደስ አላቸው፡፡ ከጌታ መከራ ተካፋይ በመሆናቸው ኩራት ተሰማቸው፡፡

ጠላት ለወጣቶቹ ሴቶች የተቀበጠጭ ጊደር አዘጋጅቶላቸው ነበር፡፡ ተዋጊዋ ጊደር በስቴዲየሙ ታሪክ ታይታ አትታወቅም ነበር፡፡ አመራረጣቸውም ጾታዋ ከሴቶቹ ጋር እንዲስማማ ተድርጎ ነበር፡፡ ሴቶቹን ልብሳቸውን ገፈው ከጊደሯ ጋር መረቡ ውስጥ ከተትው ለዘግናኝ ትርዒት አቀረቧቸው፡፡ አንደኛዋ ልጅ ገና ቀንበጥ ወጣት መሆኗን፣ ሌላዋ ደግሞ ጡቷ የሚንጣባጠብ ትኩስ አራስ መሆኗን ያየው ሕዝብ ጭካኔውን መቋቋም ስላልቻለ ትዒቱ እንዲቆም ጠየቀ፡፡ እንደ ገና ተመልሰው መቀነት አልባ ቀሚስ እንዲያደርጉ ተደረገ፡፡

ጊደሯ መጀመሪያ የወጋችው ፐርፕቱዋን ነበር፡፡ በጀርባዋ ተዘረጋች፡፡ እደምንም ቀና ብላ ከሚደርስባት መከራ ይልቅ ክብሯን ለመጠበቅ ወደ ጎን ተቀዶ ጭኗን ያጋለጠውን ቀሚስ መሰብሰብ ጀመረች ፡፡ በቀመጠልም በዚህ የድል ሰዓት ጸጉሯ ተመስቃቀሎ እንዳትሞት እና በሐዘን የሞተች እንዳትመስል የጸጉር ማስያዣ እንዲሰጧት ጠየቀች፡፡

ከዚያም ተነስታ ቆመች፡፡ ፌሌሺያ የተሰኘቸው አገልጋይዋ መሬት ላይ እንደ ወደቀች ስላየች ወደ እሷ ተጠግታ እጇን ይዛ አነሳቻት፡፡ በልብ ሙሉነት አጠገብ ላጠገብ ቆሙ፡፡ ደም የጠማው ሕዝብ በደረሰባቸው ስቃይ እንደጎርፍ በወረደው ደማቸው ስላልረካ ከዚያ መረብ ውስጥ እንዲወጡ ተደረገ፡፡

ፐርፕቱዋ ከአዳዲስ ክርስቲያኖች ጋር ቆሞ እንባውን እያዘራ የሚመለከታትን ወንድሟን በምልክት ጠርታ «በእምነት ጽኑ፡፡ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ፡፡ እኛ ካለፍነበት ከዚህ ነገር የተነሳ እምነታችሁ እንዳይደክም፡፡» አለችው፡፡

… ወዲያውኑ ትርኢቱ ወደ ማብቂያው ስለተቃረበ ነብር ተለቀቀባቸው፡፡ በህልሟ እንዳየችው መምህሯ ሳታውረስ ነብሩ አንድ ጊዜ ሲነክሰው ደሙ ተንዠቀዠቀ፡፡ ራሱን ፈጽሞ የሳተ ቢሆንም አንገታቸው ወደሚቀላበት ቦታ ወረወሩት፡፡ ሕዝቡ ግን በድናቸው ፊት ለፊት አንዲቀርብ ጠየቀ፡፡ ስለዚህም ስማዕታት በራቸው ፍቃድ እርስ በእርሳቸው በፍቅር አሳሳም እየተሳሳሙ መስዋዕትነታቸው ፈጸሙ፡፡ ብዙዎቹ በአንገታቸው የሚያልፈውን ሰይፍ ዝም ብለው ተቀበሉ፡፡ ሳታውራስ በመሰላሉ ላይ መጀመሪያ እደወጣ ሁሉ በሰማዕትነትም ማንም አልቀደመውም፡፡ ቀድሟት በመሄድም ፕርፐቱዋን እየጠበቃት ነበር፡፡

ፕርፕቱዋ ግን ገና መከራዋን አልጨረሰችም ነበር፡፡ አጥንቷ ላይ የሰይፍ ምት ሲያርፍ በከፍተኛ ድምጽ ጮኸች፡፡ ለጊዜው ይች ሞትን በጀግንነት የተጋፈጠች ሴት ያለ ፈቃዷ የማትሞት መሰለች፡፡ የሚንቀጠቀጠውን የግዙፉን የግላዲያተር ሰይፍ ወደ አንገቷ መራችው፡፡ ይሄች ታላቅ ሴት ያለፍቃዷ ማንም ሊገላት የማይችል መሰለ፡፡

በእርግጥም ለጌታችን ክስስ ኢየሱስ ክብር የተመረጡ የተባሉት እውነት ነው!

[የፐርፕቱዋ ባልና ልጅ እጣ ፈንታ ምን እንደ ሆነ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡]

Advertisements

ምን ሐሳብ አለዎት?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s