Uncategorized

ግጥም ሸማች ዘማሪዎች ያስፈልጉን ይሆን?

የዝማሬን  ጅማሬ ለማሰተንተን ከየት ጀምረን የት መሄድ እንዳለብን አላወቅም። የመጽሐፍ ቅዱሳችን አንድምታ ግን “ዝማሬ” ቅደመ ፍጥረት እንደ ተጀመረ ያመላከታል። እርግጥ ነው ከእኛ ቀድመው የተፈጠሩ መላዕክት የእግዚአብሔርን ዙፋን በዝማሬ መላዕክት ሳያንቆጠቁጡት አልቀረም። ከድህረ ፍጥረትም በ`ላ የብሉይ ኪዳን ምስክርነት ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳየን እስራኤላውያን ራሱን ከገለጠላቸው አምላክ ጋር የሚያወሩበት ቋንቋ ዝማሬ እንደ ሆነ ነው።[i] ለዚህም በዘጸዐት የተዘመረውን የማርያምን መዝሙር እንደ ጅማሬ አንስተን በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ እሰከ ጠቀሱት ዝማሬዎች መዝለቅ እንችላለን። በጥቅሉ መጽሐፍ ቅዱሳችን ዝማሬ ከእገዚአብሔር ጋር መነጋገር ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ የምንጠቀምበት ቋንቃ ነው። (ለነገሩ አዳምም የመጀመሪያውን ዝማሬ የዘመረው ለሄዋን ነው!)

ባለፕሮቴስታንት ዘውግ ዝማሬ ምናልባት በቀደምት ሚሲዮናውያን ዘመን ሳይገባ እንዳልቀረ ይገመታል። ለወጋችን እንዲበጀን ቅደመ ኢሕአዲግ እና ድህረ ኢሕአዲግ ብለን በግርድፉ ከፍለን ማየት አንችላለን ። ቅደመ ኢሕአዲግ የነበሩ ዘማሪዎች በግርድፉ ዝማሬ ከእግዚአብሔር ጋር የሚማከሩበት አሕዛብን የሚመክሩበት የውስጥ ብሶታቸውን የሚገልጡበት፣ ፖለቲካ አጀንዳቸውን የሚያንጸባርቁበት አይነተኛ መሳሪያ ነበር። የዚህ ዘመን ዝማሬዎች ያልዳሰሱት ጓዳ እና ጎድጓዳ አልነበረም። ከዚህ ዘመን ዝማሬዎች ዋነኛ ባህሪያት መካከል ዋነኛው ከዝማሬ የሚገኝን ክፍያ (የቤተ ክርስቲያንን ፖስታ አይጨምርም!) አለመቀበል እና “ ይህንን ዝማሬዬን ለቤተ ክርስቲያን ማሰሪያ ሰጥቻለሁ” የሚል ነበር የምነሰማው።

ድህረ ኢሕአዲግ ስንመጣ  ዝማሬ “ፈንጠዝያ” ማዕከል ያደረገች እና በገንዘብ ምሕዋር ላይ የምትሽከረከር ሆነች። ከጥቅት በአቋማቸው ከጸኑ አዳዲስ መዘምራን በስተቀር አብዛኞቹ መዘምራን በዝማሬ  ይዘት እና ገንዘብን በመቀበል ረገድ ያላቸው አቋም አንድ አይነት ነው። በገንዘብ ረገድ ያለቸው አቋምም እቅጯን እንደራደር የሚል አይነት ነው። አንዳንዶቹ ቤተ ክርስቲያንን ሰአይቀር በዋጋ ይሞግታሉ ያሉኝ ወዳጆቼ አሉ።  ይባስ ተብሎ ደግሞ ከሰሞኑ አንድ የፌስ ቡክ ወዳጄ ያስታወቀኝ ደግሞ ግጥም እየገዙ መዘመር ጀምረዋል (እንደሚሰጣጡ የምናውቅ ቢሆንም!)  የሚል ነው።

የዚህ ጽሑፌም ዓላማ ግጥምን ገዝቶ መዘመር ነውር ነው ወይ የሚል ነው? እነዚህን ግጥም ሸማች ዘማሪዎች ምን እናድርጋቸው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማፈላለግ “እንዴት ተደርጎ” የሚሉ ወገኖች የሚያነሱትን  ተቃውሞ እና የእኔን አመለካከት ኩልል አድርጌ አሳያለሁ።

ግጥም ሸማች መዘምራን አያስፈልጉንም  የሚሉ ወዳጆቼ የሚያቀርቡት የመጀመሪያ ተቃውሞ።  ግጥም ገዝቶ መዘመር ዘፈን ያስመስለዋል የሚል ነው። የዘፈን ግጥም ከጌታ ይሰጣል እንጂ እንዴት ይገዛል ሲሉ ይሞግታሉ። ዘፋኞች ግጥም ገዝተው ይዘፍናሉ ፤ ስለዚህ ዘማሪዎችም ግጥም ገዝተው ከዘፈኑ ምኑን ተለያዩ  መንፈሳዊነቱስ የቱ ላይ ነው?

ሁለተኛው ደግሞ ግጥም ከተገዛ  “ለዛውን”  ያጣል የሚል ነው። ግጥሞች ለአማኞች በረከት የሚሆኑት ከግለሰቡ ልምምድ ፈልቀው በሰውየው (ሴትየዋ) ቋንቋ ተፅፈው ሲቀርቡ ነው ይላሉ። ግጥም ለአንድ ሰው ከጌታ የሚሰጥ መልዕክት ነው፤ ያንን መልዕከት ደግሞ ማስተላለፍ ያለበት ግለሰቡ ራሱ ነው። የምን ግጥም ሸመታ ነው ወግዱልን ይላሉ።

በእነዚህ እና ሌሎች ተጓዳኝ ምክንያቶች ላይ ተመስርተው ወዳጆቼ። የመንፈሳዊ መዝሙሮች ይዘት እና ለዛ የጠፋው ከዚህ የተነሳ ነው ሲሉ ይደመድማሉ። አንዷ ወዳጄ “እነዚህን ዘፈኖች…ገዝቼ የማዳምጥበት ጉልበት የለኝም..አብነት ሙት ..ጥሩ ዘፋኞቹ እኮ ይበልጥ መንፈሳዊ ሊሆኑ ነው?” ብላኛለች።

እኔ ግን በሁለቱም የተቃውሞ ሃሳቦች አልስማም። ለምን አትሉኝም። ለአንድ ክርስቲያን ግጥም መግጠምም ሆነ መዘመር የእግዚአብሔር ሥጦታ ነው። እንዳንድ  የድምጽ ሥጦታው ያላቸው ወገኖች ግጥም ላይ አቅም ያንሳቸዋል። የግጥም ሥጦታው ያላቸው ሰዎች  ደግሞ ድምጹ ያጥራቸዋል። ባለ ድምጹ ይግጠም፤ ባለገጥሙ ይዘምር ብለን የ“ጨበራ ተዝካር” ልናድርገው ካለሰብን በስተቀር አይሆንም።  ስለዚህ በጋራ በመረዳዳት እግዚአብሔርን ቢያገለግሉ ምን ክፋት አለው?

እርግጥ ነው የ“ንግድ ልውውጡ” ላይ ግን ገደብ ይኖረኛል። ገጣሚዎች ልክ እንደማንኛውም ሰው  ሚያስፈልጓቸው ነገሮች አሉ። ለእነዚያ ነገሮች  ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ነገር ግን ሙልጭ ብለው  “አለአግባብ” ንግድ ውስጥ ከገቡ ግን የእግዚአብሔር ጸጋ ነጋዴዎች ከሚለው ክስ አያመልጡም። ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተሰጣቸወን ሥጦታ በአግባቡ ካቃመሱን እነሱም ከዘማሪ ወገኖችጋር በአንድነት  ከእኛ ገንዘብ  ቢቃመሱ ምን ክፋት አለው።

ግጥም ከተገዛ ለዛውን ያጣል የሚለው አመለካከት ነው። እርግጥ ነው ጌታ ግጥምን ሊሰጥ እንደሚችል ባልክድም ግጥም ከተገዛ ለዛውን ያጣል በሚለው ሐሳብ ግን አልስማማም።  ግጥም ምንጩ ጌታ ከሆነ ፣ ጌታ ደግሞ መልዕከቱን የሰጠው ሰው ለኖሮው የሚያስፈልገውን ነገር ለመሟላት ገንዘብ መቀበል ምን ክፋት አለው? ራሳቸው ጽፈው ይዘምሩ ከሆነ ደግሞ ከላይ ከጠቀስኩት ምክንያት ባሻገር ትውልድ ላለፉት ዘመናት ሲዘምረው የኖረው መዝሙረ ዳዊት በሌላ ሰው የተጻፈ እንጂ እኛ የፃፍነው አይደለም። (በዕስትንፋሰ እገዚአብሔር እንደተጻፈ እርግጥ ነው!) ነገር ግን ዘማሪዎቻችን (ጌታ ልቦና የሰጣቸው!) ያንን መዝሙር በዚህ ዘመን እንደ አዲስ እንድንኖረው ይረዱናል። ስለዚህ ግጥሙ ጌታን የሚያከብር እስከ ሆነ ድረስ  እና የተዘመረው ጌታን በሚያከብር ሰው እስከ ሆነ መገዛት አለመገዛቱ ልዩነት የሚፈጥር አይመስለኝም። ምናልባት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዘማሪያን ዘንድ የምናየው ግጥም መሰጣጠት (በተለይም በቅርብ ታዋቂ የሆነችው ዘማሪ) ገንዘብ እንዳለበት የሰማሁት ነገር እውነት ከሆነ እማኝ ለመቁጠር ሩቅ መሄድ አያስፈልግም።

ወዳጆቼ ካላይ ከጠቀሷቸው ምክንያቶች ጋር በማያያዝ የመዝሙር አቅም የደከመው ዘማሪዎች “ገንዘብ ወዳድ” ስለ ሆኑ ነው ይላሉ። እኔ ደግሞ የምለው ለዝማሬዎቻችን (አብዛኞቹ) “ጣውላ ጣውላ” ማለት ምክንያቱ ከጌታ ጋር ያለ ግንኙነት መድከም እና ሁሉም በየስጦታው አለማገልገሉ ነው ባይ ነኝ። ዝማሬማ “እርስዎም ይሞክሩት” ነው የሆነው። የደፈረ እና ገንዘብ  ለው ሁሉ መዝሙር እያወጣ ነው።

እውነቱን ለመነጋር እነዚህ ግጥም ሸማች መዘምራን  ያስፈልጉናል። ነገር ግን ከሙግታችን ባሻገር እነዚህ “ለአደጋ የተጋለጡ” ወገኖቻችን ወደ ጌታ ብናቀርባቸው ፣ ብንገስጻቸው፣ አገልግሎታቸውን “ኦሪጂናል” በመግዛት ብንደጉም፣ አንዳንዴ ደግሞ ብንረዳቸው። ጌታ ወደ ቀደመው ክብሩ ባይመልሳቸው ከምላሴ ጸጉር ይነቀል።

ይህን ሐሳብ በሙግት እንድናጠራው የሚፈልግ ካለ ጽሁፉን ይሰደድልኝ ለማውጣት ዝግጁ ነኝ። አስተያየት ያለችሁም ሰዎች ከዚህ በታች ብታሰፍሩልኝ እሰየው ።

ለሥም አጠራሩ ምሥጋና ይግባው!


[i] William A. Vengeremen, Psalms: Zemndorvan NIV Bible commentary (v2), (pradis electronic edition ,200)

Advertisements

ምን ሐሳብ አለዎት?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s