Uncategorized

የሐዊ ማስታወሻዎች- ክፍል 8

ነሐሴ 2003

አይኖቹ ጉልበተኛ ናቸው።  ዘርዘር ያሉ ጥርሶቹን ብልጭ እያደረገ በስስት አይን ሲመለከተኝ ፈገግታው ውስጤን አናወጠው። ከግራ አይኑ ጥግ አምስት ሳንቲም የምታህል ጠባሳ እንዳለበት ያያሁት ዛሬ ነው። ጸጉሩ ሙልጭ ብሎ ተላጭቶ መሐል አናቱ ላይ ትልቅ የቁስል ፕላስተር ተለጥፎበታል። ከሲጋራ እፎይ ብሎ የሠነበተው ከንፈሩ ድርቅ ብሎ የነቃቃ ኮትቻ መሬት መስሏል። ክስት ብሎ በሪሞት ኮንትሮል የሚንቀሳቀስ እንጂ በራሱ አቅም የሚጓዝ አይመስልም። ጌታ የሰው ልጅን ከፈጠረ በሃላ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ሲልበት ያለው ቅርጽ ይህ መሰለኝ። ብቻ ምን አለፋችሁ ፈገግታው ጠቅላላ እንቅስቃሴው በውስጤ አንጀትን የሚያላውስ ስሜት ሲዘራብኝ ይታወቀኛል።

“ሐዊ ከሞን እዚህ ድረስ እኮ መምጣት አልነበረብሽም?” አለኝ ያንን ጉልበተኛ ፈገግታውን እየሳያኝ።  ዙሪያው ያሉ እስረኞች ቅላቸውን ስለተላጩ ኦፕራሲዮን ክፍል ውስጥ ሊገቡ የተዘጋጁ ሕመመተኞች ይመስላሉ።

“ቤዝ..በእኔ የተነሳ እኮ ነው..” አልኩት የልልምጥ ፈገግታ እያሳየሁት (ኪኪ ባስነሳችው ጸብ የተነሳ እስር ቤት ከገባ ይኸው ድፍን ሁለተኛ ወሩ… ከዚህ በፊት በሥርቆት ተሳትፈሃል ተብሎ እዚያው ይቆይ መባሉን ነገሮኛል።  አሁን ቤዛ የወደቀ እቃ እንኳን ያነሳል። እንኳን ሊሰርቅ። እርግጥ ነው መጽሐፍ ምናምን ሊሰርቅ ይችላል። ንጥቂያ ግን እማየ ትሙት አያደርገውም!! ብቻ ምን አለፋችሁ..ይኸው እስር ቤት ነው ያለው!)

“አቦ አትጨናነቂ …ዳዲ ቅዳሜ መጥቼ አስፈታኸለሁ ብሎኛል”አናቱን በእጁ አከክ አከክ አድርጎ

“አንቺ ሠላም ነሽ አይደል ምድብ ወጣ እንዴ… ኪኪ እንዴት ነች?”

“ኦ ለካ አልሰማህም አብረን ነው የተመደብነው… ካራማራ ትምህርት ቤት ..”

“አትቀልጂ!”

“ቤዝ ሙት!!” አልኩት በእጄ ወደ ያዝኩት ሳህን እያመለከትኩ።

በእጄ የያዝኩትን ሳህን ላሳልፍለት እጄን ስሰነዝር “ማነሽ እዚያ ጋር  ፍተሻ አለኮ” አለችኝ ድምጿ ከድምጽ ማጉሊያ እንጂ ከጉሮሮዋ የሚወጣ የማትመስል ሴት። ወደ `ላ የተጎነጎነችው ጸጉሯ ያለቀ መወልወያ መስሏል። የለበሰችው የፖሊስ መለያ የታጣበው ኢሐዲግ አዲስ አበባ ሳይገባ በፊት ይመስላል።

“ይቅርታ!” አልኩና ፈጠን ብዬ አቀበልኳት።

ልክ ቆሻሻ ውስጥ ምናምን እንደሚፈልግ ልክስክስ ውሻ ሳህኑን ከፍታ ፊቷን ከስክሳ ትኩር ብላ ተመለከተቸው። የምትፈትሽ ሳይሆን የምግቡን ንጥረ ነገር ለማወቅ የምትመራመር ነው የምትመስለው። ዝም ብዬ ሳያት የትህትና ማነስ እንደሚታይባት ጠረጠርኩ። (አባዬ “አንዳንድ ሰዎች እራሳቸውን ዝቅ አድርገው ስለሚመለከቱ ስለጣን ስትሰጫቸው አላግባብ ይጠቀሙበታል..ስለዚህ አንቺ ስለራስሽ ትክክለኛ ግምት ሊኖርሽ ይገባል..አንቺ የጌታ ልጅ ነሽ። የእኔ ልጅ ነሽ!” የሚለኝ ነገር ውልብ አለብኝ።)

ትኩር በንቀት ስትመለከተኝ ያሰብኩትን የሰማች መስሎኝ ጉልበቴ ተንቀጠቀጠ “አንተ ና ቅመስ !” አለች ወደ ቤዛ እየተመለከተች። ቤዛ ያለምንም ፍራቻ ተጠግቷት እጁን ሰዷ ከሳህኑ ውስጥ ብቅ ሲል የእኔን ምሳና እራት የሚያክል ጉርሻ ተሸክሟል(ፖሊሷ እንዳትቆጣሁ ፈራሁ!)። ምናልባትም ሁለተኛ ጉርሻ እንደማያገኝ ቀልቡ ሳይነግረው አልቀረም።

ልክ ሳህኑ ዞር እንዳለ በግምት አምስት የሚሆኑ እስረኞች በአንድ ጊዜ እጃቸውን ወደ ሳህኑ ሰደዱ ። ሳህኗ ባፈጢሟ ስትከተል እያንዳንዱ እሥረኛ አንዳንድ ጉርሻ ደረሰው።  ቤዛ ዳር ቆሜ ትኩር ብሎ ያያቸዋል። ‘ሰሞኑን ገባ የተባለው ድርቅ እዚህ ነው እንዴ ያለው!’ ብዬ አሰብኩ። ቤዛ አሳዘነኝ። (አሳዘነኝ አበዛሁ መሰለኝ..ብቻ አሳዘንኝ ከእናንተ አልደብቅ በጣም አሳዘነኝ!!!)። ከቆምንባት በስተግርጌ ያለች ጣሪያ ግድግዳዋ ቆርቆሮ የሆነች የማደሪያ ክፍል በዚህ የክረምት ወቅት ፍረጅ እንደምትሆን አሰብኩና ቤዛ (ሌሎቹንም እስረኞች ጨምሮ ከእሱ ባይበልጥም) አሳዘኑኝ። ኪ ኪ ኪ ኪ ኪ ወይኔ ጉዴ!

በዚህ ላይ ደግሞ  ፖሊሶች መረጃ ሲፈልጉ እንደሚኮሮኩሟቸው ስሰማ አንጀቴ ተላወሰ። ዝቅ ብዬ የዛችን ትዕቢተኛ ፖሊስ ጫማ  አየሁና አንድ ጊዜ በዚህ ጫማዋ ብትለኝ ብናኝ እና ትናኝ  ነበር የምሆነው። አንደኛ ለምንድን ነው የሚመቷቸው? ማለቴ ሰብዓዊ መብት ምናምን እያልን ስንማር የከረምነው ነገር በተግባር አይሰራም ማለት ነው። እሺ ሌላው ይቅር እግዚአብሔር እንዴት እነዚህ ትንንሽ ልጆች ዱላ ሲጠግቡ እንዴት ዝም ይላል። የእገዚአብሔር ዝምታ ግን እሰከ መቼ እንደሆነ አይገባኝም። ዳዲ “እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ይናገራል እኛ ስለማንሰማው ነው። ይላል። ግን የታለ ደምጹ የታለ በተግባር  የሚታደገው።

ለካ ዳዲ ሁል ጊዜ እስረኞችን ጠይቁ እያለ የሚያስተምረን አለመታሰራችን ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ሊያሳየን ነው። ወይስ ደግሞ የጌታን ፍቅር ለእነሱ እንድናካፍላቸው። ኦኬ እንደዛ ከሆነ ደግሞ እነዚህስ ፖሊሶች ጌታን አያውቁትም ። ጌታን የሚያውቁት ከሆነ ለምንድን ነው እነዚህ እሰረኞች የሚደበድቡት።

ለነገሩ ጥፋተኛ እራሴ፤ በእኔ ጦስ አይደል ይሄ ልጅ እዚህ የገባው። ማለቴ አርፌ ብቀመጥስ። ለነገሩ እኔ ምን አጠፋሁ ያቺ ጦሰኛ ኪኪ ነች እዚህ ውስጥ የከተተችው። ለነገሩ ነው እንጂ እሷስ ምን አጠፋች? በእሷ ምክንያት እዚህ ቢገባም …ወንጀል ፈጽሟል መባሉ ነው እዚህ እንዲቆይ ያደረገው።

“ሴትዬ ሰዓት አልቋል እኮ ነው የምልሽ!” ሳህኑን ይዘ አጠገቤ አፍጥጣ ቆማለች።

“አትሰሚም ሰዓት አልቋል እኮ ነው የምልሽ”

ልቤ ለጥቂት ደቂቃ መቀሟን ብቻ አስታውሳለሁ። ቤዛን ቻው ሳልለው ሳህኔን ሰብስቤ ውልቅ ብዬ ወጣሁ:፡

Advertisements

ምን ሐሳብ አለዎት?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s