መጣጥፍ Articles

ኢየሱስ አያቴን ይመስለኛል …

ኢየሱስ አያቴን ይመስለኛል።
ይህች አያቴ የእናቴን ጡት ሳልጥል አንስታ ያሳደገችኝ ሩህሩህ እና አዛኝ ሴት ነች። አያቴ ኮሌጅ አልበጠሰችም እዚህ ግባ የሚባል ትምህርተ ሐይማኖትን አልቀሰመችም። በኑሩ ደረጃዋም የልጅ ልጅ ለማሳደግ የሚበቃ ገቢ ያላት አልነበረችም። “እናየውም ዘንድ የደም ግባት” አልነበረውም የሚለው ቃል የሚገልጣት የብዎቻችሁን እናት ወይም አያት የምትመስል ሴት ነበረች። መንደራችን ሰዎች “የአባቡ እናት” እያሉ ነበር የሚጠሯት።

ወደ ትውልድ መንደሬ አስልሼ ስሄድ አንዳንድ አያቴን የሚያውቁ የመንደራችንን ሴቶች አገኛለሁ። ልክ እንደ ትንሽ ልጅ አገላብጠው ይስሙኝ እና እንዲህ ይሉኛል። “አንተ አንድ ፍሬ ልጅ ዛሬ አድገህ አያትህ እኮ ከእንሥራቸው ጋር ተሸክመው ነው ያሳደጉህ!” ይሉኛል። እርግጥ ነው የተወለድኩት ውሃ በእንሥራ ከአዲስ አበባ ቦኖ ውሃዎች በሚቀዳበት ዘመን ነው። አያቴ ከእንሥራ ጋር እንዴት ትሸከመኝ እንደነበር ለማሰብ ብሞክር የማይቻል ሆነብኝ። ይህንን ነገር ግን በርካቶች ይሉት ስለ ነበረ እውነትነቱን መካድ ተሳነኝ። አያቴ ከእነሥራዋ ጋር ትሸከመኝ ነበር!
ይሄ ብቻ ግን አይደለም። አያቴ ትወደኛለች። ይቅርታ ታዲያ በወሬ አይደለም የምትወደኝ ነፍሷ እስከ መስጠት ድረስ። (ደፋር አትሉኝም!) አስታውስላሁ አያቴ በሰማኒያዎቹ ዕድሜ በምትገኝበት ጊዜ አፍላ ጎረምሳ ነበርኩ። ማመሻሽትን እየተለማመድኩ ነበር። አያቴ ልክ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ሲሆን አጥርተው በማያዩ አይኖቿ ትኩር ብላ አላፊ አግዳሚውን እየተመለከተች መጥታ አደባባይ ላይ ቆማ ስትጠብቀኝ አስታውሳለሁ። ደሞ ከእኔ ብሶ ሳያት እበሳጫለሁ እንጂ አመስግኛት አላውቅም። የሠፈር ሰዎች “ጎረምሳ እኮ ነው !” ምን ይሆናል እያሉ ሲያሽሟጥጧት አስታውሳለሁ።
ሠፈራችን የአቦ ቤተ ክርስቲያን ራስጌ ጉብታው ላይ ነው። በየወሩ በአምሥት አካባቢው በ”የኔ ቢጤዎች” ይጥለቀለቃል። ታዲያ በልጅነቴ “የኔ ቢጤ” እፈራለሁ። (ምናልባት ስለ ጭራቅ እየተነገረኝ ስላደግኩ ይሆን እንዴ!) ። ታዲያ አያቴ በጠዋት ከዘራዋን መዥረጥ አድርጋ እኔን ወደ ትምህረት ቤት ለማድረስ ትነሳለች። የዚያን ሰዓት እንደ ጦር የምፈራቸው “የኔ ቢጤዎች” አንሰው አንሰው የጤፍ ፍንካች አክለው ይታዩኛል።
የእኔ መታመም በቤታችን ውስጥ ሽብር ከሚፈጥሩ በርካታ ነገሮች መካከል አንዱ ነበር። የእኔ መታመም ለአያቴ የእሷ ሕመም ነበር። አስታውሳለሁ ። ከጠበል ፣ ከእመቱ ፣ከውዳሴ ማርያም ከሁሉ አንዱም አይቀራትም ያ ካለተሳካላት። ቡናውን ታፈላ እና ሪሚጦውን ትረምጥ እና ጥቁር ወሰራ ዶሮዋን በአናቴ ላይ አሽከርክራ ትለቃታለች። ብቻ በሷ እውቀት እና በእሷ መረዳት ህይወቴን ይታደጋል ያለችውን ሁሉ ታደርግ ነበር።

ዛሬ ዛሬ ያለሁበት ቦታ ላይ ቆሜ ሳስባት “በዚህ ብላቴና ልጅሽ ምትክ ሕይወትሽን ስጪ!” ብትባል ምትሰጥ ይመስለኛል።
እነዚህን ሁሉ ሳስብ እንዲህ እላለሁ። አያቴ ወደ ኢየሱስ ሙላት መምጫ መንገዴ እግዚአብሔር የተጠቀመባት “ሞግዚት” ናት ብል ሐሰት የሚለኝ ሰው ይኖር ይሆን? ወጣም ወረደ ግን በአያቴ ውስጥ ድብዝዝ ያለ ቢሆንም የኢየሱስ ፍንካች ነበር።

(ማስታወሻነቱ የዚህ ዓለም ጣጣ ሲያልቅ እና የክብር ጌታ ሲመጣ ፊት ለፊት እንገናኛለን ብዬ ለማምነው ለማፈቅራት አያቴ የአባቡ እናት (እማማ ጽጌ) ፦ ለአባቡ እናት 2003)

Advertisements

One thought on “ኢየሱስ አያቴን ይመስለኛል …

ምን ሐሳብ አለዎት?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s