Uncategorized

የሐዊ ማስታወሻዎች (The Dairies of Hawwii) ክፍል ስድስት

ሐምሌ 2002

“አስቀያሚ ቀን!” አልኩ ድምፄን ወጣ አድርጌ። ሰማዬ ጥቁር ብሎ ያስፈራል። በየደቂቃው የሚያሰማው የጉርምርምታ ድምፅ “ምኑን አይታችሁ?”የሚል ይመስላል። ካፊያው የለበሰኩትን ቀይ ወፍራም ባለፀጉር  ጃኬት ዘልቆ እየገባ ማጅራቴ አካባቢ ያርሰኛል። የዝናብ ዘለላዎች በቅዝቃዜ የደነዘዘ ፊቴ ላይ ያርፉና አፍንጫዬ ላይ ተንጠልጠለው ቁልቁል ይወድቃሉ። ያደረግኩት ጉልበት ድረስ የሚደርስ ጥቁር ‘ቡትስ’ ጫማ ምንም የሚያግደው ነገር የለም። ከሰፈራችን ቀይ ጭቃ አንስቶ በየአስፋልቱ መሐል እሰካሉት ትናንሽ ኩሬዎች ድረስ እየደረማመሰ፣ እያንቦረጫጨቀ፣ እየጨፈላለቀ ይሄዳል። ከቀጠሮዬ ሰላሳ ደቂቃ ያህል አሳለፌያለሁ። በዕዝነ ህሊናዬ ኪኪ ጎሸን ካፍቴሪያ ቁጭ ብላ በንዴት ስትብከንከን ታየኝ። ማታ የዓለም ዋንጫን ጨዋታ ሳይ አሰከ ዕኩለ ሌሊት አመሸሁ። ከዛ ዕንቅልፍ ጣለኝ ? “እንቅልፍ የሞት ታናሽ ወንድም ነው” ትል የለ ማሚ!  

ትላንት ማታ ዳዲ እና ማሚ የአዳር ፀሎት ስለነበረባቸው ወደ ደብረ ዘይት ሄደው ነበር። እኔና ቤቢ ከእግር ኳስ በፊት ፊልም ስናይ ነበር ። ‘ዘ ኖት ቡክ’ በጣም ደስ የሚል ፊልም ነበር ። አንድ አፍቃሪ ባል በመርሳት በሽታ የተያዘች ሚስቱን በወጣትነት ዘመናቸው ያሳለፋቸውን የፍቅር ጊዜያት እንድታስታውስ በሆስፒታል ውስጥ የሚያደርገውን ጥረት ነው። በተለይ ልጆቹ ወደ ቤት ና ሲሉት “እናታችሁ ቤቴ ናት። ከሷ ተለይቼ የት እሄዳለሁ?” ሲል “ዋው”! አንድ ቦታ ደግሞ ተለያይተው ሲገናኙ ሲሳሳሙ ከዛ በ¹ላ ደግሞ …. ሲያደርጉ ። የሚገርመው ዕኔ አፍሬ አንገቴን ሳቀረቅር ቤቢ ግን እየሳቀ ይመለከት ነበር። የሰውየው ፅናት ያስገርማል። እውነት እንዲህ አይነት ወንድ ይኖር ይሆን ? አላውቅም ? ‘ቸርች’፣ ትምህርት ቤት የማውቃቸው ወንዶች በህሊናዬ  በየተራ አሰብኳቸው። ድንገት ከመሐላቸው ታዬ ከንፈሩን በምላሱ እያራሰ ያየሁት መሰለኝ እና ዘገነነኝ ። እንደሱ አይነት ወንዶች በጣም ያናድዳሉ! የዓለም ሴቶች ሁሉ የዕነሱ ቢሆኑ እንኳን አይጠግቡም !

          ከገባሁበት የሐሳብ ሸለብታ የነቃሁት አንድ ‘ቦልስ’ መኪና “ሲጢጢጢጢጢጢጢጢጢጢጢጢጢጢጢጢጥ” ብሎ ገፋ አድርጎኝ ሲቆም ነበር። በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች ከሊስትሮዎች ጀምሮ ኬክ ቤቱ በረንዳ ላይ እስከ ነበሩት ሰዎች አካባቢውነ በጩሀት አደበላለቁት። ሾፌሩ  አንገቱን በመስኮት አውጥቶ የሚችለውን ያህል ስድብ ሲያዘንብብኝ እግሬ ተብረከረከ። በድንጋጤ ተንዘፈዘፍኩ። በድን እግሬም እየጎተትኩ ወደ ካፍቴሪያው መራመድ ጀመርኩ።  በቅርብ ርቀት የነበሩት ለማኟ እትዬ ሺምርጫሽ  “ውይ የእኔ ልጅ አፈር በበላሁ …. ምን ያሳስብሻል! አንቺ ለራስሽ አንድ ፍሬ ልጅ!” ሲሉ ይሰማኛል። ሊስትሮዎች አሽሟጠጡ ፣የታክሲ ረዳቶች ተራገሙ።  ተንደርድሬ  ወደ ካፍቴሪያው ውስጥ ገባሁ።

ካፍቴሪያው ውስጥ ኪኪ ተረጋገታ እግሮቿን ወንበር ላይ ሰቅላ ኬኳን እየገመጠች ነበር። ስታየኝ ቀና ብላ የንዴት ፈገግታ አሳየችኝ። ካፍቴሪያ ውስጥ የተቀመጠው ሰው ሁሉ በተለይ ወንዶች ትኩር ብለው ያዩኝ ስለነበር አረማመዴ ጠፋብኝ። አጠገቧ ስደርስ ወንበር  ስቤ በቁሜ ወደኩበት። አስተናገጇ ተቀምጬ እንኳን ሳልደላደል መጥታ “ምን ልታዘዝ ?” አለችኝ። ቀና ብዬ አይን አይኗን እየተመለከትኩ ዓይኖቼን ጭፍን ጭፍን በማድረግ አሰብኩ። ወይ ጉድ! ልጅቷ አፏን ከፍታ እየተበቀችኝ ነው። እኔ ምርጫ ከአዕምሮዬ ጠፍቷል። ኪኪ “አይስ ክሬም” ብላ ገላገለችኝ። ደጋግሜ በረጅሙ በመተንፈስ ራሴን ለማረጋጋት ሞከርኩ። ኪኪ ማብራራያ በሚፈልግ አይነት ትኩር ብላ ትመለከተኛለች። በአንድ እጇ የያዘችውን ኬክ እየገመጠች ፤ በአንድ ዕጇ ደግሞ በሞባይሏ‘ጌም’ ትጫወታለች፣ ጆሮዋ ላይ ነጭ የ ‘አይ ፖድ’ ፣የጆሮ ማዳመጫ ይታያል። ሁሉም ዐዲስ ናቸው ! በጥቅሉአዲስ የተከፈተ “ቡቲክ” መስላለች።

( ኪኪ ይህንን ሁሉ ገንዘብ ከየት ነው የምታመጣው አትሉኝም? ከእናቷ! የኪኪ እናት በሰፈራችን ከማውቃቸው ሐብታሞች አንዷ ነች። በየጊዜው ዱባይ ትመላለሳለች፡፡ በተመለሰች ጊዜ ለዕኔና ለኪኪ የልደት ቀናችን ነው የሚመስለን። ስትሔድ ለኪኪ ብር አሸክማት ነው የምትሄደው፤ ስትመለስ ደግሞ ለሁለታችንም ልብስ ይዛልን ትመጣለች ። ታዲያ የምታመጣቸው ልብሶች ዳዲ ሳያያቸው የሚደረጉ ናቸው ከታዩ ስቅላት ነው የሚፈረደብኝ። ስለዚህ የፈለግነውን ማድረግ የሚያስችል ብር አለን ማለት ነው። ያስቃል አይደል? በ17 ዓመቷ እኛ ትምህርት ቤት እየተማረች፣ ዕኛ ሰፈር እየኖረች፣ ብዙ ብር ያላት ልጅ ኪኪ ትመስለኛለች! ምናልባት በሳምንት የምታጠፋው የአቶ ዝናቡን የወር ደሞዝ የሚያህል ይመስለኛል። የልጅ ሐብታም! ኪኪ አባቷ አይታወቅም ። እናትየዋ ‘ዱርዬ’ ነገር ናት። ሲጋራ ታጨሳለች፣ ጫት ትቅማለች፣ የተለያዩ ወንዶች ወደ ቤታቸው ሲመጡ አያለሁ።  እኔን ግን ልክ እነደ ነፍሷ ነው የምትወደኝ፤ አንዳንዴ ከኪኪ በላይ የምትወደኝ ይመስለኛል? )

ድንገት ከ¹ላዬ አንድ እጅ እንቅ ሲያደረገኝ በድንጋጤ ከመቀጫዬ ተነሳሁ ጋዜጠኛው ቤዛ ነበር። ሳየው ለምን እንደሆነ የማላውቀው ደስ የሚል ስሜት ተሰማኝ። ኪኪን እጁን ዘርግቶ ከጨበጣት በ¹ላ ወንበር ስቦ አጠገባችን ተቀመጠ። ፀጉሩ ያለወትሮው አድጎ፤ በሰማያዊ መደብ ላይ ነጭ ነጠብጣብ ባለው ሻሽ ታስሮ የቤተ ክርስቲያን ጉልላት የተሸከመ ይመስላል። አይኖቹ ከወትሮው የበለጠ አንሰው ሊጠፉ የተቃረቡ ይመስላሉ። ካፊያው ከላይ የለበሰውን ፀጉራም ሹራብ ላይ ሲያርፍ የፈጠረው አቧራ ቀመስ ጠረን፤ በቅርብ ጊዜ ካጨሳት ሲጋራ ጋር ተዳምራ አፍንጫችንን ሰነፈጠችን። ሁሉ ነገሩ ጠፍቶ የቀረው ብልጥ ፈገግታው ብቻ ነው። ሳቅ ብሎ “እንዴት ነው ታዲያ ?” አለ ዓይን ዓይናችንን አፈራርቆ እየተመለከተ። ኪኪ ኮስተር አለች።

“ ‘ፒስ’ ነው… አንተ እንዴት ነህ ቤዝ አልኩት?”

እጁ ላይ የያዘውን የኦሾን መፅሐፍ በቆረጣ እያየሁ። ቤዛ የስብሐት እና የኦሾ አድናቂ ነው። በህይወቴ እንደ ቤዛ መፅሐፍ ማንበብ የሚወድ ሰው አይቼ አላውቅም። ባለው ጊዜ አንዳንዴም ከትምህርት በበለጠ ጋዜጦችን እና መፅሐፍትን ይከታተላል። እንደሰማሁት አባቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስለሚያስተምሩ መፅሐፍ ያመጡለታል ይባላል። ብቻ ቤዛ “ቡክ ዎረም’  መፅሐፍ አንብቦ የማይጠግብ ነገር ነው። የሱ የንባብ ሱስ እኔ ላይ ተጋብቶ እኔም ባለኝ ጊዜ ቤዛ የሚያመጣልኝን መፅሐፍት ፣ጋዜጦች መፅሔቶች አነባለሁ። መፅሓፍ ቅዱስን ፣የኦሾን እና የስብሀትን መፅሐፍ ዕኩል ያነባል።  ዕብድ ነገር ነው። የፈለገውን የሚያደርግ እንደፈለገ የሚኖር ለሰው ግድ የማይሰጠው አይነት ሰው ነው። (እንዲያውም አንድ ጊዜ የሰፈራችንን ልጆች ልብስ ምን ያደርጋል ብሎ አሳምኗቸው ራቁታቸውን እንዳስኬዳቸው ሲወራ ሰምቻለሁ።) ባይገርማችሁ ‘ቸርች’  እንሂድ ስለው እንኳን ሳያቅማማ ነው አብሮኝ የሄደው። ግን ምን ያደርጋል እነ ስብሐትን ማንበቡንም ሱሱንም ቀጥሏል።

“አለሁልሽ በጣም ተጠፋፋን ያንን ፅሁፍ እንዴት እያደረግሽልኝ ነው?” አለኝ።

ፈገግ ብዬ በአንድ አይኔ ጠቀስኩት። ኪኪ ስለ ‘ሐዊ ማሰታወሻዎች’ ምንም ነገር አታውቅም። ለምንድን ነው ያልነገርኳት፤ ነፃ መሆን ስለምፈልግ ወይም…ብቻ እኔ እንጃ ! ለኪኪ የደበቅኳት የመጀመሪያው ነገር ነው።

“ይገርምሀል በጣም ነው የወደድኩት….በተለይ መግቢያውን” ዋሸሁ። ጓደኛዬን ከማጣ ምናለበት…ብቻ ፊቴ በሐፍረት ቀላ። ኪኪ ሁለተኛውን ኬክ  በሹካ ቦጭቃ ወደ አፋ ሰደደችው።

ቤዛ “እሺ ልጅት ታዲያ ዕንዴት ነው?” አላት የውሸት ፈገግ ብሉ ኪኪን ዓይን ዓይኗን እንደ ‘ሰፒል’ በሚዋጉ አይኖቹ እየተመለከተ።። ቤዛ “ታዲያ ዕንዴት ነው?” ማለት ልምዱ ነው። በተለይ ወሬ ሲያልቅበት እና ነገር ሲፈልግ ‘ታዲያ ዕንዴት ነው?’ ይላል። ኪኪ ፊቷ ተቀያየረ። ስትናደድ እንደምታደርገው በጥርሶቿ ከናፍሮቿን መነካከስ ጀመረች። ፊቷ ላይ ያሉት መዋቢያዎች ስፍራቸውን መልቀቅ ጀመሩ። አፍንጫዋ የወትሮ ዳንሷን ጀመረች። ቤዛ እና ኪኪ አይዋደዱም። ቤዛ ኪኪን “ሲጨምቁት እንደሚጮህ አሻንጉሊት ቁም ነገር ሲወራ ትጮሀለች” ሲል፤ ኪኪ ደግሞ “ይሄ መወልወያ ራስ ካለ መፅሐፍ ምንም አያውቅ.. አንቺ  ግን ምኑ ተመችቶሽ ነው?” ትላለች። ሁል ጊዜ አይጥ እና ድመት ናቸው አይዋደዱም።

“ ‘ኢንጆይ’ እያደረግኩ ነው!” አለች በምፀት ፈገግታ ታጅባ።

“እህ… በጣም ደስ ይላል… ‘ኢንጆይ’ ነው ያለሽኝ!” አለት ሳቁ ከንፈሩ ላይ ተንጠልጥሎ።

“ያ” አለችው ኪኪ ሽሙጡ ገብቷት። ለራሴ “ ፍልሚያው ተጀመረ” አልኩ።

“ ‘ላንጉጅ’ እንዴት ነው ባከሽ?” አለ ወደ ዕኔ ዕየተመለከተ

“አሪፍ ነው!” አልኩት ፡፤

“ዓረብኛ  ነው እንዴ የምትማሩት …እንግሊዘኛ መስሎኝ?” አላት እናቷን ለማሽሟጠጥ እንደሆነ ገብቷት በገነች።

“ዕንዴት?” አልኩት ፍልሚያው እንዲፋፋም ፈልጌ።

“ማለቴ ‘አሪፍ’ የአረብኛ ቃል ይመስለኛል ?” አለ። ኪኪ ለቀቀች። ከመቀመጫዋ ተነሳች።

ሰዓቷን ትኩር ብላ ተመልክታ “ አንሄድም ረፍዷል” አለችኝ።

“እህ አይስ ክሬሜስ?” አለኳት ኮስተር ብዬ።

ቤዛ  ከት ብሎ አንደ መብረቅ የሚያስገመግመውን ሳቁን አንዴ ሲለቀው ከካፍቴሪያው ባለቤት ጀምሮ በረንዳ ላይ እሰካሉት ሰዎች ድረስ ፊታቸውን አዙረው ተመለከቱን። ኪኪ ድፍን ሐምሳ ብር ጠረጴዛው ላይ ጥላ እየተንደረደረች ካፌውን ጥላ ወጣች።

ለቤዛ ሐምሳ ብሩን አቀብዬ ስመለከታት መሐል አስፋልቱ ላይ ደርሳለች። ድንገት ሁለት ወጣቶች ወደ ዕሷ ተጠጉ አንደኛው እጇን እንቅ አድርጎ ይዞ ፤ኪኪ ለማስለቀቅ ስትፍጨረጨር ተመለከትኳት። ከአንደኛው ጎረምሳ እጅ አምልጣ ስትወጣ ሌላኛው ጎረምሳ ያዛት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ታመናጭቀው ጀመር አሁን ችግር ሊፈጠር መሆኑ ስለገባኝ ለመጠጋት መንደርደር ጀመርኩ ። ድንገት የጥፊ ድምፅ ሲጮህ ተሰማኝ። በደመነፍስ ይመስለኛል ተንደርድሬ ኪኪን የመታትን ፍልጥ የሚያክል ጎረምሳ የሸሚዝ ኮሌታውን  ይዤ አነቅኩት አንድ ጊዜ በጥፊ አቀመስኩት። በጥፊ ከተመታው ልጅ አጠገብ የነበረው ሴቶችን በማስጨነቅ የሚታወቀው አሞ የሰደደው ጥፊ ግራ ጉንጬ ላይ ሲያርፍ ብልጭ የሚል ብርሃን ተከትሎ አገጬ ከስፍራው ሲነቃነቅ ተሰማኝ ። ሁኔታው ተደበላለቀ በአከባቢው የነበሩ ሰዎች ሁሉ ግር ብለው ወደ ዕኛ ሮጡ።

ከዛ በ¹ላ የማስታውሰው ነገር ቤዛ ተንደርድሮ መጥቶ እኔን ከመታኝ ጎረምሳ ጋር ሲተናነቅ  ድንጋይ የያዙ ሊስተሮዎች ቤዛን ሊቀጠቅጡት እየተሳደቡ ሲጠጉ፣ ኪኪ አንደኛውን ልጅ በጥፍራ ልትዘነጣጥለው ስትንደረደር ፣ ከየአቅጣጫው ሰዎች ሁሉ ሲሰባሰቡ። ድንገት አካባቢው ላይ ያለው ነገር ሁሉ ይሽከረከርብኝ ጀመር። ሰዎቹ ሁሉ ይሽከረከራሉ ፣ ሰማዩም መኪናውም ኬክ ቤቱም ሁሉም ነገር ይሸከረከራሉ። ጨለማ ሽክርክሪት ፣ጨለማ ሽከርክሪት የሰዎቹ ድምፅ ክፉኛ እየራቀ መጣ፤ ወደ መሬት ተመዘገዘግኩ መሬት ስደርስ፤ ጭንቅላቴን አስፋልቱ ላይ እንደኳስ ሲነጥር የሰራ አካሌን የሚነዝር ህመም ተሰማኝ።  ከዚያ በ¹ላ  ከቤዛ “ሐዊ ..ሐዊ..ሐዊ” ከሚል ድምፅ በስተቀር አንድም ነገር አልሰማሁም።

Advertisements

One thought on “የሐዊ ማስታወሻዎች (The Dairies of Hawwii) ክፍል ስድስት

ምን ሐሳብ አለዎት?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s