መጣጥፍ Articles

አቶ ሰለሞን ፡- እኛ ክርስቲያኖች ስለ ፖለቲካ “አያገባንም”!!!

አንድ አንጀት አርስ መጣጥፍ በአውራ አምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ያነብብኩት ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 26/2002 ዓ.ም ነበር ። ሰለሞን ሞገስ በተባሉት ፀሐፊ የተፃፈው  ይህ መጣጥፍ አንድ ታዋቂ ዘፋኝ ስለ ፖለቲካ የሰጠውን “አላዋቂ” አስተያየት መነሻ በማድረግ “ይህ ብሂል [ፖለቲካ አያገባኝም] የብዙዎች መጠለያ(ዋሻ) ሆናልና” ሲሉ “ፖለቲካ አያገባኝም” የሚለውን አስተሳሰብ ይሞግታሉ። አጠቃላይ መጣጥፉን እንደታነቡ እየጋበዝኳችሁ ለዚህ ፅሁፌ መነሻ የሆኑኝን ዋና ዋና ጉዳዮች ልጠቃቅስ። በተጨማሪም “እኒህ ‘ፖለቲካ አያገባንም’ የሚሉ ሰዎች ስለ ኔልሰን ማንዴላ ክብር ባርኔጣቸውን ያነሳሉ። ጋንዲንም ሆነ ማርቲን ሉተር ኪንግን አብዝተው ያደንቃሉ ።…” “በውስጥም በውጪም የሚያደንቋቸው እነዚያ ሰዎች ግን ፖለቲከኞች እንጂ ቄሶች ወይም ሼሆች እንዳልነበሩ አስታዋሽ ይፈልጋሉ።” በመቀጠልም በ“በበኩሌ ስለ ሐይማኖት ዕሳቤ ለሌሎች የማካፍለው የበሰለ ዕውቀት የለኝም”  (አፅንዖት የእኔ) በማለት ያለሳልሱና የሚከተለውን ሐሳብ ይሰነዝራሉ “በክርስትና ዕምነት መፅሐፍ ግን የናዝሬቱ ኢየሱስን ለማጥመድ ፈልገው ስለቄሳር (ግብር)  ጠይቀውት። “የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሄር የቄሳርን ለቄሳር” ማለቱን አስታውሳለሁ። ልብ በሉ “የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር …” ብሎ “የቄሳርን ለቄሳር  አለ እንጂ…”[i]። የዚህች አጭር ፅሁፍ ዓላማም እነዚህን ሁለት ሐሳቦች ማሰተንተን እና መሞገት ነው።

ሰለሞን እራሳችው  “ስለፖለቲካ አያገባኝም” ለሚለው አስተሳሰብ መንስዔ ያሉትን “የፖለቲካን ምንነት እና ትርጓሜ ስህተት”መሆኑን ስለ ጠቀሱ ትርጓሜ በማስቀመጥ ልጀምር።  ከሆነ በካምብሪጅ ኦንላይን መዝገበ ቃላት መሰረት  ፖለቲካ (politics)፦

ሐገር እንዴት መመራት አለበት የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ  መንግስት፣ የህግ አርቃቂ አካላት እና ግለሰቦች  የሚያሳድሩት ተፅዕኖ፣ በመንግስት ውስጥ ስልጣን የመያዝ ሂደት ፤ ሐገሪቷ እንዴት መመራት እንዳለባት የሚያጠና መስክ፤ የግለሰብ ፖለቲካ የምንለው ደግሞ ሐገር እንዴት መመራት አለባት በሚለው ዙሪያ ግለሰቦች ያላቸው አስተሳሰብ፤ የአንድ ቡድን ወይም ድርጅት ፖለቲካ ደግሞ ጥቂት ሰዎች ስልጣን እንዲይዙ የሚያስችል ውስጣዊ የዕርስ በዕርስ ግንኙነት ነው። (ትርጉም በእኔ)

በተጨማሪም ሌላው አለም ዓቀፍ መዝገበ ቃላት ሚርያም ዌብሰተር ኦን ላይን መዝገበ ቃላት ይህንኑ ፖለቲካ (Politics) የሚለውን ቃል ሲፈታ፦

የመንግስት ጥናት ሳይንስ ወይም ጥበብ፣ የመንግስትን ፖሊሲን በመምራት እና በማሰተዳደር ጉዳይ ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር  ጥበብ ወይም ሳይንስ፣ ስልጣንን በማሸነፍ የማግኘት ሳይንስ ወይም ጥበብ፣ ፖለቲካዊ  ድርጊቶች፣ ልምምዶች ወይም ፖሊሲዎች፤ፖለቲካዊ ጉዳዮች፣ ለስልጣን እና ለመሪነት በተፎካካሪ ቡድኖች እና ግለሰቦች መካከል የሚደረግ ውድድር፤ ፖለቲካዊ ህይወት (እንደ ስራ)፤ ማታለል እና ቅንነት በሚጎድላቸው መንገዶች የሚደረግ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ፤ ግለሰብ ፖለቲካዊ አመለካከት፤ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦች ውስብስብ ግንኙነት፣ ከፖለቲካ አንፃር የሚታዩ ጠባዮች እና ተግባቦቶች (የብሔር ፖለቲካ፣ የፖለቲካ ቢሮ) (ትርጉም በእኔ) 

 

ከላይ ካስቀመጥኳቸው ትርጓሜዎች (ሌላ ትርጉም ከፈለጉ የሚከተለውን ይመልከቱ።)በመነሳት በግርድፉ የምንደርስበት ድምዳሜ ፤ ማንም ሰው “ፖለቲካ አያገባኝም” ቢልም እንኳን በፖለቲካ ውስጥ እንደሚኖር ግልፅ ነው። ከዚህም አንፃር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ሰዎችም ሰው እንደ መሆናቸው መጠን ፣ እንዲሁም በእነዚህ ፖለቲካዊ መስተጋብሮች ውስጥ  የሚሳተፉ እንደ መሆናቸው “ፖለቲካ” ያገባቸዋል። (“አያግባንም” ቢሉም ያም የእነሱ ፖለቲካ ነው! )

ከላይ በጠቀስኩት መልኩ ሲታይ አቶ ሰለሞን “ቄሶች ወይም ሼሆች” የምትለውን አባባል የተጠቀሙባት በሽሙጥ መልክ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ምናልባትም “ቄሶችና እና ሼሆች” በፖለቲካ ውስጥ አያገባቸው ይሆናል የሚል መነሻ ሐሳብ የተነሳ ይመስለኛል ። ለዚህ ምላሽ የሚሆናቸው በፖለቲካ “ትርጓሜ እና ምንነት” ዙሪያ የሰነዘርኩላቸው ሐሳብ የመጀመሪያው ነው። አስከትዬ ደግሞ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ላንሳ፦ ለመሆኑ አቶ ሰለሞን ማርቲን ሉተር ኪንግ ማን እንደሆኑ ያውቃሉ? ማርቲን ሉተር ኪንግ ቄስ ናቸው።(ዊኪፔዲያን ይመልከቱ .) ለፖለቲካዊ ተግባራቸው መነሻ የሆናቸው ደግሞ ከመፅሐፍ ቅዱስ ጉያ የተቀዳው ስለሰው ልጆች ዕኩልነት ያላቸው አመለካከት ነው። አለፍ እንበል ከተባለም የደቡብ አፍሪካውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ አቡነ ዴዝሞንድ ቱቱ ማንሳት ይቻላል። ከዚሁ ከሐገራችን ደግሞ በደርግ ዘመነ መንግስት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማሳማታቸው የተገደሉትን ቄስ(ደ/ር) ጉዲና ቱምሳን ማንሳት ይቻላል። በእርግጥ በእኛ ሐገር በዚህ ዘመን የሚገኙ “ ቄሶች” ድምፃቸው  አይሰማም ለማለት ፈልገው ከሆነ  በደንብ ተቀብያለሁ።

አቶ ሰለሞን የእነዚህ ዘመናዊ ቄሶች (ወንጌላውያንን ብቻ) ቸልተኝነት መፅሐፍ ቅዱስም ሆነ የወንጌላውያን ክርስቲያናዊ አስተምህሮን የሚወክል አይደለም። ለዚህ ዕስቲ ጥቂት ማስረጃዎችን ልጠቃቅስ ፦

የክርሰቲያናዊ ስነ መለኮት እና ስነምግባር መምህር የሆኑት ቤኔት እንዲህ ይላሉ፦

“ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር እንደሆነ በሚያምኑት በዚህ ዓለም ውስጥ መኖር ፣መወሰን እና መተግበር መቻል አለባቸው። ሁልጊዜም በእገዚአብሔር ፍርድ ፊት ይቆማሉ ፤በተጨማሪም እግዚአብሄር ሁሉንም ባህል ፣ ሁሉንም ስልጣን፣ ሁሉንም ማህበረሰብ፣ ሁሉንም ሐሳብ እና ሁሉንም ቤተክርስቲያን  በላይ እንደሆነ በመረዳት በዚህ ተስፋ ውስጥ ይኖራሉ።”[ii]

ኬኒያዊው ኦኩሉ  ፈረንሳዊውን የስነ መለኮት አዋቂ አንድሬ ዱማስን በመጥቀስ እንዲህ ይላሉ፦

“ፖለቲካ ማለት በንቃት በአብሮነት ውስጥ መካፈል ማለት ከሆነ ፤ የዓለም ሁሉ ጌታ እንደጠራው እና እንዳስነሳው ሰው ሁላችንም በፖለቲካ ውስጥ ‘ንቁ’ ተሳታፊ ነን።…በተጨማሪም እንዲህ ሲል መከራከሪያውን ያቀርባል፤ ቤተክርስቲያን ከፖለቲካዊ ምህዳር ልትሸሽ የማትችልበት ምክንያት ቤተክርስቲያን ይህንን ካለዳረገች የግለሰብ ብቻ ሐይማኖት ስለሌለ ለሁሉም አንድን ሐይማኖት መስበክ ስለማትችል ነው።”[iii]

አቶ ኤልያስ በቀለ ክርስቲያን እና ፖለቲካ፦ በፖለቲካ ውስጥ የሚኖረው የቤተ ክርስቲያንና የክርስቲያኖች ተሳትፎ[iv] በሚለው መፅሐፋቸው  ቤተ ክርስቲያን ከፖለቲካ በምንም አይነት ሁኔታ ማምለጥ እንደማትችል እና ብቸኛው አማራጯ በፖለቲካ ውስጥ ተገቢውን ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሆነ ያሰረግጣሉ። በተጨማሪም ሌላው አሜሪካዊ ፀሐፊ ጆን ኤድሰሞ በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ለቤተክርስቲያን በጣም አስፈላጊ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ቤተክርስቲያን ለማህበረሰቡ በምን አይነት ሁኔታ አስተዋፀኦ ማበርከት እንደምትችል የተለያዩ ዘዴዎችን ያመለካታሉ። (ምናልባት ወደፊት ይህንን ጉዳይ እንቃኘው ይሆናል።) በጥቅሉ ማለት የፈለግኩት የዚህ ዘመን “ቄሶች” ንቁ ተሳታፊ አይደሉም ማለት ቤተክርስቲያን ወይም የሐይማኖት ሰዎች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ሊያደርጉ አይገባም ማለት አይደለም።

እስቲ አሁን ደግሞ  “በተለይ የሐይማኖት ሰዎች በፖለቲካ ጉዳይ አያገባንም ይሉ ይሆናል።” ለሚለው  እንደ ማጠናከሪያ በሚመስል መልኩ ያሰፈሩት የመፅሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እንመርምረው። የመጀመሪያው ሐሳብ ከማቴ22፡15-22 /ሉቃ.20፡20-26/ማር.12፡13-17 ካለው ክፍል ውስጥ የተወሰደ ነው። ሙሉ ሐሳቡን ስነመለከተውም በተለይ በማርቆስ ወንጌል የተጠቀሰው ግለፅ እንደሚያደርገው ለኢየሱስ የቀረበ “ወጥመድ” (ከዚያም እንዲያጠምዱት ከፈሪሳውያንን እና ከሄርዶስ ወገን ሰዎችን ላኩ።”) ነው። ጥያቄያቸውም ይህንን የተበከለ ውጥናቸውን ለመተግበር የተደረገ ነበር፤ “ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም!” እኛስ እንክፈል ወይስ አንከፈል?” ይሄ ጥያቂ ከዐውዱ ወጥቶ ስንመለከተው የጥያቄው አስቸጋሪነት ግልፅ አይሆንልንም።

በዚያ ዘመን  ኢየሱስ የተከተሉት አበዛኛዎቹ ሰዎች በሮም ግብር የተመረሩ ነበሩ። በተጨማሪም ቀናተኞች የሚባለው ቡድን አባለት ለሮም መንግስት በምንም አይነት ግብር መክፈል የለብንም የሚሉ ሰዎች ነበሩ። በተቃራኒው ደግሞ ከሳሾቹ ግብሩን ባይወዱትም ይቀበሉት ነበር። ኢየሱስ የገባበትን አጣብቂኝ እስቲ እንሳበው! “መክፈል ይገባል!” ቢል ከአብዛኛው ተከታዮቹ ጋር ያጣሉታል፤ ህዝቡ ከተቃወመው ደግሞ እነሱ ለመያዝ እና ለማስገደል ይቀላቸዋል። “መክፈል አይገባንም!” ቢል በአጭሩ መንግስትን ተቃወሟል ለሚለው ክሳቸው ማስረጃ ይሆናቸዋል። አጣብቂኝ! በዚህ አውድ ውስጥ ኢየሱስ ዲናር አንሰቶ አሳይቷቸው ምስሉ የማን እንደሆነ የሚጠይቃቸው ። እነሱም “የቄሳር” ይሉታል! በዚህም ጊዜ “የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእገዚአብሔር ስጡ” አላቸው። ኢየሱስ ማለት የፈለገው እያንዳንዱ ሰው ከመንግስት የሚጠበቅበትን ሃላፊነት (ግብር መክፈል) መውጣት አለበት፤ ከእግዚአብሔር የሚጠበቅበትንም ሐላፊነት መወጣት አለበት። እነዚህ ሁለቱ አብረው መሄድ የሚችሉ ናቸው። ነገር ግን የእግዚአብሄር እና የመንግስት ሐሳብ በሚጋጩበት ጊዜ የእግዚአብሔርን ሃሳብ መመረጥ እንደሚገባን በሌሎች የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሰፊ ማብራሪያ የተሰጠበት ነው።[v]

ስለዚህ ከላይ በሰጠሁት ማብራሪያ መሰረት ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን አባባል የተጠቀመው ከመንግስት  የሚጠበቅብንን ሃላፊነት መወጣት ከእግዚአብሔር የሚጠበቅብንን ሐላፊነት መወጣት አለብን ለማለት ነው። በግርድፉ የመፅሐፍ ቅዱስን አስተምህሮ ስነመለከት ግን ከዕምነታችን ጋር የማይጋጭ እስከሆነ ድረስ ከመንግስት የሚጠበቅብንን ሐላፊነት መውጣት አለብን የሚል ነው።[vi] ይህ እንዲህ ከሆነ ደግሞ እሳቸው እንደማረጋገጫ ከሰጡት የሚከተለው ምሳሌ ጋር ለመስማማት ይከብደኛል።

“የየካ ሚካዔል አለቃ የነበሩት አባ መርሻ ወ/ ማሪያም  ወራሪው ጣሊያን አገራችንን በግፍ በያዘና ህዝብን ባሰቃየ ጊዜ እኚህ መስቀል የጨበጡ አባት

ወግጅልኝ ድጓ ፤ ወግጅልኝ ቅኔ

ወንዶች ከዋሉበት መዋሌ ነው እኔ። ሲሉ ተቀኝተው እና ታላቅ የአርበኝነት ተግባር አከናውነው መስዋዕታቸውን ታሪክ ዘግቦ አቆይቶልናል። አገር እና ነፃነት ከሌለች ሐይማኖት የለችምና።”

አንደኛ ፤ ይህንን ታሪክ በውል (አውዱን ማዕከል) አድርጌ ባለውቀውም  “ሃይማኖት” በጦርነት ጊዜ ወደ ጎን ተትቶ ጦርነት መዘመት አለበት በሚል መንፈስ ተጠቅመውበት ከሆነ አልስማማም። ምክንያቱም ለሐገር ሉዓላዊነት መፋለም እና እምነት ያለቸውን ልዩነት ግልፅ ስላለሆነ ነው።  ለዚህ ግልፅ ማስረጃ የሚሆነን በአድዋ ጦርነት ጊዜ ታቦታት ከየደብራቸው ወጥተው ከሰራዊቱ ጋር መዝመታቸው  እና “ሐይማኖታዊ” ሐላፊነታቸውን እሰከ መወጋት ድረስ የተወጡ መሆኑ የሚያሳይ ነው። ሁለተኛ፤ “አገር እና ነፃነት ከሌለች ሐይማኖት የለችምና።” የሚለው አባባል ከመፅሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር አልተጣጣመልኝም። “ሃይማኖትን” የፈጠርናት እኛ የሰው ልጆች አይደለንማ! ለእኔ የማምንበት ነገር ሁሉ ከእግአብሔር ዘንድ (በቃሉ [በመፅሐፍ ቅዱስ]  እና [በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ] የተገለጠ  ነው። ይህም መልዕክት የሚገድበው “ሐገራዊ ሁኔታ የለም”  ዕምነታችን የበቃለችው ለእግዚአብሔር ታማኝነታቸውን ለመግለጥ ደማቸውን በዘሩ ሰማዕታት ላይ ነው። ይህንን ስል ታዲያ “ሐገር እና ነፃነት” አያስፈልጉም ለማለት እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። (በወንጌላውያን ክርስቲያኖች ላይ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ላይ የደረሰው እና እየደረሰው ያለው ጭፍጨፋ ምስክር ነው።)

በመጨረሻም እንደ አብዛኛው የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አመለካከት ፣ በተለይም እንደ መፅሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት “ቄሶች” ከፖለቲካዊ ተሳትፎ ነፃ መሆን አለባቸው የሚል አመለካከት ያለ አይመስለኝም። ነፃ መሆን ቢፈልጉም አይችሉም! ምክንያቱም ሁላችንም “ንቁ” የፖለቲካ ተሳትፎ እናድርግ እንጂ በፖለቲካ ውስጥ እየዋኘን ነው የምንኖረው። በእርግጥም እንዲህ አይነት አስተምህሮና ትውፊት ቢኖረንም “ንቁ” የፖለቲካዊ ተሳትፎ ባለማድረግ “አያገባንም” እያልን ይመስለኛል። ታደያ ጎበዝ ከዚህ ሸለብታችን ማን ይቀስቅሰን?  ለዚህ ብሎግ ታዳሚዎችና ለሌሎች ወዳጆቼ  አቶ ሰለሞን የጠቀሷትን   የኑረዲን ዒሳን ግጥም እነሆ፦

“ዕኔ ምን አገባኝ የምትሉት ሐረግ፤

እሱ ነው ያረዳት ሐገሬን እንደ በግ ፤

የሚል ግጥም ልፅፍ ብድግ አልኩኝና ፤

ምን አገባኝ ብዬ ቁጭ አልኩ እንደገና።”


[i] አውራአምባ ታይምስ ፤3ኛ ዓመት ቁጥር 122 ሰኔ 26/2002 ዓ.ም ዕትም።(ገጽ.7) በተለየ ሁኔታ ካልተጠቀሰ በስተቀር ሁሉም በጥቅስ ውስጥ የሚገኙ ነገሮች የተወሰዱት ከተመለከተው ጋዜጣ ላይ ነው።

[ii] Bennet, John C. ,Christians as citizens (Great Britain: Norwich: World Christian Books,1956)

[iii] Okullu Henery , Chruch and state :In nation Building and Human Development (Kenya,Nairobie: Uzimma Press,1987)

[iv] ኤሊያስ በቀለ፤ ክርስቲያን እና ፖለቲካ ፡በፖለቲካ ሂደት ውስጥ የሚኖረው የቤተክርስቲያን እና የክርስቲያኖች ተሳትፎ (አዲስ አበባ ኢትዮጵያ፡ ኤስ አይ ኤም ስነፅሁፍ ክፍል፡ 1996ዓም)

[v] ሮሜ13፡1-7፣1ኛ ጢሞ2፡1-6፣1ጴጥ.2፡13-17

[vi] Eidsmoe, John. God and Cesar : Christian Faith and Political Action (Westchester .Illinois: Cross way books,1989)

Advertisements

2 thoughts on “አቶ ሰለሞን ፡- እኛ ክርስቲያኖች ስለ ፖለቲካ “አያገባንም”!!!

ምን ሐሳብ አለዎት?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s