መጣጥፍ Articles

አራቱ “የሐይማኖት መቻቻል” ግብዓቶች ፦ ከኦርቶዶክስ፣ ሙስሊም እና ወንጌላውያን ወዳጆቼ እንደተማርኩት

 

ሰኔ 19-20 2002 ዓ.ም  ሳሪስ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የስልጠና ማዕከል ውስጥ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፣ ከእስልምና እና ከወንጌላውያን አቢያተ ክርስቲያናት የተውጣጣን ከ20 የምንበልጥ ወጣቶች ተሰብስበን ስንመካር ነበር ያሳለፍነው። ይህ “ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሐይማኖት መሪዎች ለልማት የስልጠናና እና  የውይይት ፕሮግራም” (Influential Religious Leaders Towards Development A Training and Discussion program) በሚል ርዕስ የተዘጋጀ እና የብሪቲሽ ካውንስል ሰፖንሰር ያደረገው የንቁ ዜጋ ( Active Citizen) መርሐ ግብር ነበር:፡ ጅማሬው መፈራራት እና በመራራቅ  ሰፈነበት ነበር። የእነዚህ ምንጮች በአብዛኛው ስለተለያዩ የእምነት ቡድኖች የነበረን “ሸውራራ” መረዳት ነው ብል አጋንን ይሆን?  አነሳሴ ግን “ፍርሐት እና ጥርጣሬን” ወደሚያስገርም ሕብረት እና መቻቻል የለወጡ እና  ለሐይማኖታዊ መቻቻል (Religious Tolerance) መሰረት ይሆናሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ነገሮች ለካፍላችሁ ነው። እነሆ …

1. የጋራ ታሪክ (Shared History) እንዳለን እውቅና መስጠት 

በመርሐግብሩ ላይ በተጋባዥነት የተገኙት  የአዲስ አባባ ዩኒቨርሰቲ የታሪክ መምህር ፕሮፌሰር ሽፈራው ፤ የኢትዮጵያ ነገስታት ታሪክ የክርስትና ታሪክ ብቻ ተደርጎ እንደሚታሰብ ገልፀው፤ ነገር ግን የሙስሊሙም ማህበረሰብ  ያበረከተው አሰተወፅዖ ግን ትልቅ እንደበረ የታሪክ መዛግብትን በማገላበጥ አሰረግጠዋል። ለዚህም በምሳሌነት  በነገስታት መካከል በተነሳው አለመግባባት በውቅቱ ከነበሩት አቡን ዕኩል ድርሻ የነበራቸውን እና በሐይማኖት ምክንያት የኢትዮጵያን ንጉስ እንውጋ በሚል የቀረበላቸውን ግብዣ አሻፈረኝ ያሉትን ሼህ አሊን ጥቅሰዋል። “ይሄ ታሪክ የጋራ ታሪካችን ነው!” ካሉ በ¹ላ አስከትለው ስለወንጌላውያን እና ስለካቶሊክ ዕምነት ተከታዮች በኢትዮጵያ ግንባታ ውስጥ ያበረከቱትን አስተዋፅዖ ያስታወሱት በሚገርም   መልኩ ነበር ። “ፕሮቴስታንቶች እና ካቶሊኮች መደበኛ ትምሀርት (በተለይም ቋንቋ) በማወቅ ቀደምት ስለነበሩ ከነገስታት አጠገብ ከኦርቶዶክስ ቤትክርስቲያን ሊቃውንት ጎን አይጠፉም ነበር።” በጥቅሉ በ‘ትክክል’ (objectively) አይስፈር እንጂ በኢትዮጵያ  ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የ “እምነት ቤተሰቦች ድርሻ” የማይተናናስ ነው።  ታደያ ጎበዝ እንደ እምነት ተቋማት በሐገራችን ያለን ቆይታ ይለያይ፣ ያበረከትነው አስተዋፅዖ በስፋት እና በጥልቀት ልዩነት ይኖረው እንጂ የጋራ ታሪክ እንዳለን የማይካድ ነው። ታዲያ ግንኙነታችንን የጋራችን በሆኑ ነገሮች ላይ ብናደርገው ተቻችሎ ለመኖር እና ሐገራችንን ለማልማት አይበጅም ትላላችሁ? እኔ ግን ተስማምቶኛል!!

2. ማንነትን (Identity) መገንዘብ

በግል ማንነታችን ባህል፣ ቋንቋ፣ እና አስተዳደጋችን የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ የማይካድ ይሁን እንጂ እንደ እምነት ማህበረሰብነታችን አብዛኛው ማንነታችን የተቀዳው ከቅዱሳት መፅሐፍቶቻችን እና ትውፊታችን (Tradition) ነው። አመለካከታችንም ከሞላ ጎደል የእነዚህ ነገሮች ድምር ውጤት ነው። እነዚህን የእምነታችንን መሰረት የሆኑ መፅሐፍትን እና ትውፊቶቻችንን  እያወቅን በሄድን ቁጥር ስለማንነታችን ያለን መታመን እየጨመረ ይሄዳል። እንዲህ አይነት ደግሞ ጠንካራ መሰረት ያለው ማንነት ካለን የራሳችንንም የሌሎቹንም እናከብራለን። በዚህ ሁኔታ ውስጥ “በጨዋ ደንብ” ለመወያየት መንገድ ይከፈታል። አንዳንዴ የምናምናቸውን ነገሮች የእምነት መሪዎቻችን ከሚነግሩን ባሻገር ቁጭ ብለን አለመመርመራችን አልፎ አልፎ ለሚታዩት ግጭቶች መነሾ የሆኑ አይመስላችሁም?

3. እንወያይ ወይስ እንሟገት (Dialogue Vs Debate)?

 ውይይት ወደ አንዳች ድምዳሜ  ሳንደርስ ወይም ደግሞ አንድ ሰው በሌላው ላይ ድምዳሜውን ሳይጨንበት የሚደረግ የመረጃ ልውውጥ ነው። ይሄም አንዳችን ስለ ሌላችን ያለንን መረዳት ጥያቄ በመጠየቅ መፈተሽ እና “ እናንተ እኮ እንደዚህ አትመስሉኝም ቀርቤ ሳየው ገባኝ” መባባል ይመስለኛል።በውይይታችን ወቅትም የተፈጠረው ይሐው ነው። ውይይት ለቀጣዩ ደረጃ መሰረት የሚሆን ነው። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ሶስት የእምነት ቡድኖች የራሳቸው የሆነ ለድርድር የማይቀርቧቸው እውነቶች አላቸው። በነዚህ ዙሪያ ውይይት ይደረጋል ብትሉኝ ለመሟሟቅ ካልሆነ ይከብደኛል። ስለዚህ እነዚህ የተለያየ እውነት ያለቸው ሰዎች ሁሉም ትክክል ሊሆኑ ስለማይችሉ ማሰረጃቸውን በማቀረብ “በጨዋ ደንብ” ይሟገታሉ።  በ“ጨዋ ደንብ” አንዱ የሌላውን ባሕሪ ሳያጠለሽ (Character Assasination)፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ስሜታዊነት ሳይንፀባረቅ፣ ምናልባትም አመክንዮን መሰረት ባደረገ መልኩ  አንዱ ሌላውን ሳይሳደብ መማገት እንችላለን ማለቴ ነው። እንዲህ ከሆነ ልዩነት ያለቸው ተሟጋቾች ከሙግታቸውንም በ¹ላ ማኪያቶ ጠጥተው እየተወያዩ ልናያቸው እንችላለን። (ለግነቱ ይቅርታ ይደረግልኝ ግን አንድ ቀን ያመይሆን እንዳይመስላችሁ!) በጥቅሉ  “ሀይማኖታዊ መቻቻልን” ለመፍጠር ውይይትም ሆነ ሙግት የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። እነዚህ ውይይቶችችን እና ሙግቶችቻን  ፍሬያማ እንዲሆኑ ግን አንድ ግብዓት ያስፈልጋቸዋል።  

4. መረዳት (Understand ing)

አንድ ብስል መሪ ነበሩ በቅርቡ እንዲህ ያሉኝ “ በግጭት  አፈታት ሂደት ውስጥ ከአንድ ወገን የተሰማ ነገር እነዳልተሰማ ይቆጠራል”፤ በሙግትም ሆነ በውይይት ውስጥ እውነቱ ይሄ ይመስለኛል። ስለአንድ እምነት ከአማኞቹ ከማጣራት ይልቅ የራሳችንን መረዳት ይዘን  መነሳት ውይይቱ ወደ ሙግት ሙግቶ ወደ ጠብ እንዲያመራ መንገድ ይጠርጋል። ታዲያ ምን እናድርግ? ከውስጥም (ከአማኞች ፣ከሊቃውንት፣ከመፅሐፍት) ከውጭም (ከመፅሐፍት እና ሶስተኛ የመረጃ ምንጮች፣ድረ ገፅ…) እናጣራ። አንድ  መጥፎ ነገር ተባለ ስነባል ፈጥነን መልስ ለመስጠት ከመቸኮላችን በፊት ነገሩን አጥብቀን ለመረዳት እንሞክር። የሰማነውን እነዳልሰማነው ቆጥረን ተጨማሪ መረጃ እናፈላልግ። በዚህ ሁኔታ እላያችን ላይ ከተጠመጠመጠሙብን  ጤነኛ ያለሆኑ ቅድመ እሳቤዎች (pre understanding) እና  ችኩል ድምዳሜዎች (Hasty generalizations) ራሳችንን ለማፅዳት እና ነገሩን ወደ ተጫባጭነት (objectivity) በቀረበ ሁኔታ ለመረዳት እንችላለን። ጠጋ ብለን “ስለዚህ ምን ታምናለችሁ?” “ይሄ ማለት ምን ማለት ነው?” ብለን ካለተወያየን እና ውስጣዊ እና ውጫዊ መረዳትን ሳንፈጠር መወያየትም መሟገትም ከጀመርን የምንደርስበት ድምዳሜ ፀብ እና ዱላ ምቻ ይመስለኛል። ምክንያቱም አንዱ ስሌላው በቂ እውቀት ስለሌለው “ሸውራራ ድምዳሜ” ላይ ይደርሳል። አባቶችስ “ከማያውቁት መልዐክ የሚያውቁት ሰይጣን” የሚሉት ለዚሁ አይደል።

በጥቅሉ በዚህ ስብሰባ የእነዚህ አራት ነገሮች ድምር ፦ የጋራ ታሪክ መኖሩን እውቅና መስጠታችን፣ ማንነታችንን ማወቃችን ፣ውይይት ( ሙግት አልነበረም!)፣ እና ስለዕያንዳንዳችን ውስጣዊ እና ውጫዊ መረዳትን መፍጠራችን ሁላችንን አጀብ አስኝቶን ነበር። ስንለያይ (ለመለያየት ከብዶን ነበር!) ያ ሁሉ መፈራራት የት እንደገባ እየተሳሳቅን ተጠያየቀን ነበር። ይህንን ስሜት ጠብቆ ለማቆየት የግል እና የጋራ ግንኙታቸን ጠብቀን እንደቀጥል የተስማማን ሲሆን ፤ ሁላችንም የሄ ውይይት በእምነት ተቋማት ደረጃ ቢሆንስ ስነባባል ነበር።

(ምስጋና፦  ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፣ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ፣ እና ከወንጌላውያን አቢያተ ክርስቲያናት ለመጡ ወዳጆቼ)

ክብሩ ይስፋ!

Advertisements

ምን ሐሳብ አለዎት?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s