Uncategorized

የሐዊ ማስታወሻዎች (ክፍል አራት)

ሰኔ 13 2002ዓ.ም

ታዬ እንግሊዘኛን ከአሜሪካውያን በላይ ይናገራል ቢባል አሜሪካንን ከፊልም በስተቀር ለማያውቁ እንደኔ አይነት ሰዎች አሳማኝ ይመስለኛል። አነጋገሩ ልክ ፊልም ላይ የምናያቸውን ጥቁር የፊልም ‘አክተሮች’ ይመስላል። ተማሪዎች “የፈረንጅ ቡዳ በልቶት ነው!!” እያሉ ያሾፉበታል። ርዝመቱ በግምት ከእኔ በእጥፍ የሚበልጥ  ያስመስለዋል። ፀጉሩ ሁል ጊዜ በስሱ የተላጨ እና ቅርፅ የወጣለት በመሆኑ እላዩ ላይ የተቀመጠ እንጂ የተቆረጠው አይመስል። ትልልቅ አይኖቹ በቡናማ ዘመናዊ መነፅሩ ስር ይንቀዠቀዣሉ። ከናፍሮቹን በየሰከንዱ በምራቁ ያርስቸዋል።  ቢያንስ በአስር እና በሃያ ደቂቃ አንዴ ‘ቻፕ ስቲክ’ ይቀባቸዋል። ብዙ ጊዜ ከላይ በጥንቃቄ የተተኮስ ሸሚዝ እና ጅንስ ሱሪ ያዘወትራል። የሚያደርገው የእንጨት ሶል ያለው ጫማ መሬቱን ሲገጨው የሚፈጥረው “ኳ.ኳ.ኳ” የሚለው ድምጽ መምጣቱን በርቀት ያሳብቃል። አለባበሱ ዝንጥ ያለ በመሆኑ ብዙ ሴቶች “ሞዴል ቢሆን ይሻለው ነበር!”ይላሉ በሹክሹክታ። በአጠቃላይ ሴቶች የሚወዱት አይነት ወንድ ነው። እሱም ይህንን የሚያውቅ ይመስለኛል። ሴቶችን ሲያናግር ጎላ ያሉ አይኖቹን ያስለመልማቸዋል። በምላሱ ከንፈሩን ደጋገሞ እያረጣጠበ  ከአንደበቱ የሚለቃቸው የእንግሊዝኛ ቃላት ሴቶች ልብ ላይ ሲያርፉ የተለየ ሙቀት ይፈጥራሉ መሰለኝ ወዲያው ሙክክ ነው የሚሉት።

ጓደኛዬ ኪኪን የገጠማት ይሄ ነው። ቋንቋ ትምህርት ቤት መመዝገቧ ከቤት ለመውጣት እንደ ምክንያት ከማገልግሉ በስተቀር ጥቅም የለውም ስትል የነበረችው ልጅ፤ ትምህርት ቤት የምትገኘው ከተረኛው ጥበቃ እኩል ነው። ታውቃላችሁ ጠዋት 1፡30 ላይ ‘ላንጉጅ ስኩል’ ከደረሰች በ¹ላ  ትምህርት ቤቱ ፊት ለፊት ስለምትቆም፤ “እዛ አስፋልቱ ዳር የምትቆመው አጭር ወፍራሟ ልጅ ጋር እንገናኝ።” እያሉ ይቀጣጠሩብሻል እያልኩ አብሽቃታለሁ። በጥቅሉ ኪኪን ጨምሮ ብዙ ታዳጊ ወጣቶች በዚሁ መምህር ፍቅር ስለሚያዙ፤ ተማሪዎቹ ‘ታዬ ሲንደሮም” ሲሉ ስም አውጠተውለታል። እውነትም የታዬ መቅሰፍት! ልክ እንደ ‘አተት’ ፈጣን እና ተላላፊ ነው። ኪኪም የ“ታዬ ሲንደሮም” ምርኮኛ ሆናለች።” በቀን ውስጥ ሳታየው ከዋለች ልክ እንደ ‘ቡና ሱስ’ ያዞራታል።

ኪኪዬ  ልክ እንደ እህቴ የምወዳት ጓደኛዬ ነች። ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ጎን ለጎን ተቀምጠን ነው የተማርነው። ኪኪ አጭር እና በጣም ወፍራም ነች። አቤት ውፍረቷን ስትጠላው እሱን ለመቀነስ ያለጠጣችው ነገር መርዝ ብቻ ነው። የቻይና ሻይ፣ ሙቁ ውሃ ዋና መጠጦቿ ነበሩ። ለጨጓራ በሽታ አጋለጧት እንጂ ብዙም መፍትሄ አልሆኗትም። ስለዚህ ስለውፍረት ሲነሳ የምሯን ትናደዳለች። ከእስፖርት አይነቶች ደግሞ ሩጫ ፣ዋና ፣ኤሮቢክስ ሞክራለች ግን ምንም ውጤት የለውም። አንዳዴ ስለውፍረቷ ታስብና ክፍት ይላታል። ትንሽ ሳቃልዳት ትፍለቀለቃለች። ኪኪ ስትስቅ ሁለመናዋ ይስቃል። ትናንሽ አይኖቿ  ይብለጨለጫሉ። ትንሽ አፍንጫዋ የሳቋን ሪትም ተከትላ እብጥ ኩምሽሽ ትላለች። የወተት አረፋ የመሰሉ በጎበዝ አናጢ የተጠረቡ የሚመስሉ ጥርሶቿ ይንተገተጋሉ። ልክ እንደ እናቷ! እሷ ግን ይሄ ሁሉ ባይኖራት እና ቀጭን ብትሆን ትመረጣለች። እኔ ስለውጫዊ ገፅታዬ ብዙ ስለማልጨነቅ እገረማለሁ።

ለኪኪዬ ዛሬም ተመሳሳይ ቀን ነው። ክፍል ውስጥ ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ የምታወራኝ ስለታዬ ነው። አሁን የ ‘ፍሪ ቶክ’ መምህራችን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያወራሉ። ማስተማር ሲጀምሩ ስማቸውን ስላላስተዋወቁን፣ብዙ ጊዜ “ዩ ኖው” ስለሚጠቀሙ ሚ/ር “ዩ ኖው” ብለን ስም አውጥተንላቸዋል። ስማቸውን በ¹ላ ቢነግሩንም ‘ሚስተር ዩ ኖው’ ን ለመድነው እና መተው አልቻልንም። አጭር እና ቦርጫም ስለሆኑ በሚያስተምሩበት ጊዜ ትንፋሽ ያጥራቸዋል። ብዙ ጊዜ ስለሚያልባቸው መላጣቸውን በነጭ መሃረባቸው ደጋግመው ያደርቃሉ ። ላባቸውንም ቾክ በነካ እጃቸው ስለሚጠርጉ በጠይም መልካቸው ላይ “ጀሶ” በከፊል የተቀባ ግድግዳ ነው የሚመስሉት። አዲስ የገቡ ተማሪዎች ገፅታቸውን አይተው ሳቃቸውን መቆጣጠር ስለሚሳናቸው ብዙ ጊዜ ከክፍል ይባረራሉ። ሚ/ር ዩ ኖው በሚያስተምሩበት ጊዜ የሚያስደስተኝ ነገር ቢኖር በአንድ ክፍለ  ጊዜ ውስጥ ምን ያህል “ዩ ኖው” እንደተጠቀሙ መቁጠር ነው። ዛሬም እኔ የሚያሰተምሩትን ነገር ረስቼ ደብተሬ ላይ ጭረት እያደረግኩ “ዩ ኖው” መቁጠሬን ቀጥያለሁ።

“37… 38….39…”

“አንቺ ሐዊ ምናባቱ ሆኖ ነው ዛሬ ያልመጣው?”

“45…46…47…” እንዳልሰማ ሆኜ መቁጠሬንም ቀጠልኩ።

“ ትላንት ምን እንዳለኝ ታወቂያለሽ?”

“53…54…56…”

“አንቺን አኮ ነው የማን ነች አይጥ!!!”

 በእግሯ እግሬን በጣም ስትረግጠኝ  “ምንድን ነው?”አልኳት ድምፄን ከፍና ረገጥ አድርጌ

ሚ/ር ዩ ኖው “ ዩ አት ዘ ባክ ቴክ ኬር !” ብለው አመልካች ጣታቸውን አወዛወዙብን። ኪኪ በድንጋጤ ኩምሽሽ አለች። ኪኪ ስትደነግጥ ክብ ፊቷ ትቀላለች ። በፊቷ አማካኝ ቦታ የምትገኘው ቁራጭ አፍንጫዋ በአየር ተሞልታ ታብጣለች። አይኗ ላይ የተቀባቸው ማስካራ አሮጌ ቤት ላይ እንደተቀባ ቀለም ይፈረከረካል። ኩሏ ከአይኗ መርገብገብ የተነሳ ይቦናል። ሊፒስቲኳ መለኩን ቀይሮ ይወይባል። የደስደስ ያለው ፊቷ ይወረዛል። ትኩር ብዬ ተመለከትኳት እና ሳቅ አፈነኝ። ስሜቴን ተረድታለች መሰለኝ ከደብተሯ ላይ አንድ ገፅ ገንጥላ በትልቁ “ጨ” ብላ ፅፋ ሰጠችኝ። እንዲህ ሲባል እንደምናደድ የሚያውቁት እሷና ቤቢ ናቸው። እጄን ሰደድኩና በቁንጥጫ ትከሻዋን አነደደኳት። “ዋይ!!” ብላ ጩሀቷን አቀለጠችው ። ሚ/ር ዩ ኖው ትግስታቸው አለቀ። በእጃቸው የያዙትን ዳስተር ከብላክ ቦርዱ ጋር አጋጭተው “ጋዴም ጌት አውት!!!” ብለው ጮሁ።  እኔና ኪኪም ልክ እንደ ሰሎግ ውሻ ኩስስ ብለን በተማሪዎች አስፈሪ አይን ታጅበን  ክፍሉን ጥለን ወጣን።

ገና በሩን ከፍተን ከመውጣታችን ኪኪ “የስ ! የስ! የስ!” ብላ በዛች አጭር ቁመቷ አደገኛ የመዝለል ሙከራ አደረገች ። ተናድጄ እየተቻኮልኩ ወደ ካፌ ሄድኩና ተቀመጥኩ። እየሳቀች ተከተለችኝና ፊት ለፊቴ ተቀምጣ በሳቅ መንፈራፈሯን ቀጠለች። ድንገት ከፊቷ ላይ  ፈገግታዋ   እንደምሽት ፀሃይ እየከሰመ ሲሄድ የአይኖቿን አቅጣጫ ተከትዬ ተመለከትኩ፤ ታዬ ከፊት ለፊቱ ሃምበርገር እና ማኪያቶ አስቀምጦ ‘ኒውስ ዊክ’ መፅሄትን ያነባል። ምን አይነቱ ነው ባካችሁ አሁንም ከንፈሩን በምላሱ ያርሳል። ኪኪ አይኖቿን በእሱ ላይ ተክላ ‘ፖዝ’ የተደረገች ነው የምትመስለው። ፊቷ አንዴ ቀይ፣ አንዴ ቢጫ፣ አንዴ ደግሞ ቡና አይነት ስትሆን ተመልክቼ ሳቄን ለቀቅኩት። በካፌ ውስጥ የሚገኙ ፈንጠርጠር ብለው የተቀመጡ ተስተናጋጆች ሁሉ በአንድ ጊዜ ፊታቸውን አዞሩ። ግማሾቹ በአግራሞት ግማሾቹ በግልምጫ ተመለከቱን!

ታዬ ከተቀመጠበት መቀመጫ ከመቼው እንደተነሳ ሳናውቅ መጥቶ አጠገባችን ተቀመጠ። ያፈቀሩትን ሴቶች እንዴት መለየት እንደሚችል እየተገረምኩ ትኩር ብዬ አያየሁ አጠናሁት። በተከፈተው ሸሚዙ ውስጥ የወርቅ ሀብል በደረቱ ፀጉር ተሸፍና ስታጮልቅ አየሁና እፍረት ቢጤ ተሰማኝ። ታዬ በጥያቄ አይነት ሁለታችንንም  እየተመለከተ “ዋት ኢዝ ሶ ፈኒ ሌዲስ?” አለን በእጁ መዳፍ ፀጉሩን እያሻሻ። ኪኪ አሁንም ‘ፖዝ’ ላይ ነች።

“ሰላም ነው ቲቸር…?” አልኩት እየተቀለሰለስኩ።

ኪኪ ከእንቅልፍ እንደሚባንን ሰው ባንና “ አዎ ልክ ነው አለች” በእፍረት የቀላ ፊቷ እንዳይታይ አቀርቅራ። አይ ኪኪዬ ስተሳዝን።  እስከዛሬ ሳውቃት እንደዚህ ሆና አታውቅም።

ታዬ ከንፈሩን በምላሱ አራሰና ፈገግ ብሉ የኪኪ አይኖች ትኩር ብሎ እየተመለከተ።

“ምንድን ነው ‘ሾርቲ’ አለ?”

ኪኪ ከረጅም እንቅልፍ አንደተቀሰቀሰ ሰው ብንን ብላ  “እእ ቲቸር ዩ ኖው..ማማ..ማለቴ ‘ፍሪ ቶክ’ ቲቸር አስወጥቶን ነው?”

“ዋው …በጥብጣችሁ መሆን መቻል አለበት ?”

ድንገት የ ‘ሞባይል’ ስልኩ የሚያምር ጥሪ አሰማች። ታዬ ከኪሱ ውስጥ አውጥቶ ከፈታት ፈገግ ብሎ የእጁን አውራ ጣት አሳየን  ከመቀመጫው በፍጥነት እየተነሳ “ኦ ሃኒ ዋትስ አፕ?” ብሎ ጥሎን ወጣ።

ኪኪ አይኖቿ በንዴት ደም መሰሉ። ኮስተር ብዬ እየተመለከትኳት “ኦ…ኦ ቅናት እንዳይሆን?” ኪኪ ተነስታ ጥላኝ እይተቆናጠረች ወጣች። ተከተልኳት። ፍጥነቷን ጨመረች እኔም ፍጥነቴን ጨመርኩ ። ጭራሽ በሩጫ ጥላኝ  ሄደች መኪና የሚዘንብበትን ትልቅ አስፋልት ግራና ቀኝ ሳትመለከት በረረች። እኔም በዝግታ ተሻግሬ ደረስኩባት። የት እንደሆነ እንኳን ሳንጠይቅ ታክሲ ውስጥ ገባን። ኪኪዬ አይኖቿ እንባ እንዳረገዙ ጎን ለጎን ተቀመጥን።

“ኪኪዬ እህ…?” አልኩ አይን አይኗን እየተመለከትኳት ። ኪኪ አንደበቷን ለመክፈት ያደረገችው ሙከራ በአይኖቿ ታቁሮ የነበረውን እንባ ቁልቁል ዘረገፈው። ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳመረረች ሳውቅ ደነገጥኩ። ተጠመጠምኩባት፤ የታክሲ ውስጥ ሰዎችን እንኳን ሳታፍር ለቅሶዋ ብሶባት እተንሰቀሰቀች ማልቀሷን ቀጠለች። ምን ብዬ ነው የማፅናናት?  አባዬ ስለፍቅር የሚጠቅሳቸው ጥቅሶች በሙሉ ወደ አዕምሮዬ መጡ። አገላብጬ ብመረምራቸውም እሷን ለማፅናናት የሚያገለግል ጥቅስ ግን ላገኝ አልቻልኩም።  ሁሉም ኢየሱስ ለእኛ ወይም ኢየሱስ ከእኛ ስለሚጠብቀው ፍቅር የሚያወሩ ናቸው። ቀጥሎ በተራቸው  ወደ አዕምሮዬ የመጡት ደግሞ በድብቅ ከማያቸው ፊልሞች ፣ ትምህርት ቤት ክላስ ውስጥ ካነበብኳቸው የፍቅር መፅሄቶች ያገኘ¹ቸው ሃሳቦች ናቸው። እነሱም ቢሆኑ ግራ የሚያጋቡ እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ ናቸው። አእምሮዬ አልታዘዝ ሲለኝ አንደበቴ መከፈት ተሳነው። መፍትሄ መስጠት እና መፅናናት እንደማልችል ስረዳ ኪኪዬን ይበልጥ እቅፍ አድርጌ ወደ ደረቴ አስጠጋ¹ት። የእምባዋ እርጥበት እጄን እና ደረቴን ሲያርስኝ ውስጤ “አንቺ ብትሆኚስ ያፈቀርሽው?” ብሎ ሞገተኝ። እውነት እኮ ነው! እኔስ ብሆን ማን መፍትሔ ሰጪ እና አማካሪ አለኝ? አላውቀውም!!!!

Advertisements

ምን ሐሳብ አለዎት?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s