Uncategorized

የሃዊ ማስታወሻዎች (Part 2)

ክፍል ሁለት

ቀን ሰኔ 21 እሁድ 12፡30

በዚህች ምድር ላይ የጥላሁን እና የማይክል መሞት የማያሳስበው ዳዲ ብቻ ይመስለኛል። በተለይ ስለማይክል ጃክሰን የማይባል ነገር የለም። ከሁሉም ነገር ግን ማይክል ብቸኛ ነበር የሚለውን ያህል ያስደነገጠኝ ነገር የለም። ሰው አለም ሁሉ እያደነቀው እንዴት ብቸኛ ሊሆን ይችላል። ያስገርማል! ያስቃልም! ማሚ ይህን ጥያቄ ብጠይቃት ምን እንደምትለኝ ታውቃላችሁ “ጌታ ስሌለው ነው?”። ዳዲንስ ብጠይቀው! ጉድ ፈላ! ዳዲ እንዲህ አይነት ነገር መስማት አይመቸውም። አባዬ እንኳን የማይክል የዘፋኙ ጉዳይ ይቅር እና የእግር ኳስ ጉዳይ ሲነሳ እንኳን አይመቸውም። ዳዲ ፋራ ስለሆነ እንዳይመስላችሁ አገልጋይ ስለሆነ ነው። ውይ የኔ ነገር እራሴን ሳላስተዋውቃችሁ መዘባረቅ ጀመርኩ አይደል። ሃዊ እባላለሁ። ትክክለኛ ስሜ አይደለም። የማንንም ትክክለኛ ስም አልጠቀምም። ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ይደብራል። የሚመጣው መስከረም 17 ዓመቴን እይዛለሁ።የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ። ጓደኞቼ ስለኔ ብዙ አስተያየት ይሰጣሉ፦ ብዙዎቹ የማለውቃቸውንም ሰዎች ጨምሮ  አይኖቻቸውን በላዬ ላይ እያንከባለሉ “አይ ቆንጅና!” ይላሉ።የትምህርት ቤት ጓደኞቼ “ከጥያቄ ንጥረ ነገር ነው የተሰራሽው!” ይሉኛል።በጣም የሚቀርቡኝ ሰዎች ደግሞ “ፈላስፋ ቢጤ ነሽ !” ሲሉ ይቧልታሉ።ደፋር ወንዶች እና አይን የበሉ ሴቶች ደግሞ “ቁጭ አንጆሊና ጆሊን …ለምን ሞዴል አትሆኚም?” ይላሉ አይኖቻቸው በጉጉት ከጉድጓዱ ወጥቶ ሊነከባለል እሰከደርስ ድረስ አፍጥጠው። ይሄ እነኳን ምናልባት ረጅም ስለሆንኩ ይሆናል።ቤዛ ጋዜጠኛው ጓደኛዬ ብቻ ነው፤ “የስነፅሁፍ ሰው ወይም ፈላስፋ እንደምትሆኚ አልጠራጠርም። ምነው እንዳንቺ የመጠየቅ ሱስ በያዘኝ” ይላል። ሳቅ ብዬ “አታካብድ” ብዬ እመልስለታለሁ።ኪኪዬ ነፍስ ነገር ምን እነደምተለኝ ታውቃላችሁ “ሞጥሞጣ የ ‘ፈረንሳይ’ ልጅ !” አታስቅም።እናንተ የትኛው ውስጥ እንደሆናችሁ አላውቅም።

ዳዲ የትንሳኤው ችቦ የሚባል ቤተክርስቲያን ፓስተር ነው።በጣም ረጅም ፀጉሩ ገባ ያለ ሁልጊዜ ሱፍ የሚለብስ እና ትልቅ ጥቁር የእጅ ቦርሳ የሚይዝ ሲራመድ ፈጥን የሚል፤ከሰው ጋር ሲያወራ ትከሳ መታ መታ የሚያደርግ ሰው ፈረንሳይ ለጋሲዮን ማዞሪያ አካባቢ ካያችሁ ያ ሰው ምናልባትም ዳዲ ነው።ዳዲ የአካባበው ሰዎች ከህፃናት ጀምሮ እሰከ አዋቂዎች ድረስ ይወዱታል። የቸርች ህፃናት “የፓስተር አማረ ልጅ!” ይሉኛል። የትምሀርት ቤታችን ተማሪዎች ስለሰበካቸው ስብከቶች ፣ስለእኛ ቤት ስለሰጣቸው ምሳሌዎች ያወሩኝና። “ግን እውነት ነው?” ብለው ይጠይቁኛል። ምን አይነት ደፋሮች ናቸው ባካችሁ። ዳዲ ፈፅሞ አይዋሽም። ለምን እንደዛ እንደጠየቁኝ ሳስበው ግን ይገርመኛል። የሚዋሹ ሰባኪዎች አሉ እንዴ ? ኦሆ ምን አገባኝ። አባቢ ይወደኛል። ነገር ግን የእሱ ፍቅር ልክ እንደ ሌሎች ማታ ሲገቡ ኬክ ይዘው እንደሚገቡ፣ ልጆቻቸውን እሽኮኮ እንደሚያደርጉ አባቶች አይደለም።ዳዲ እቤት ሲሪየስ ነው። ታዲያ እንዴት አወቅሽ አትሉኝም ? እኔ እንጃ ! የምጠይቀውን ነገር ስለሚያሟላልኝ ይሆናል። ይሄ ግን የፍቅር መገለጫ ይሆናል እንዴ? አላውቅም ! እሺ ለማንኛውም የሚወደኝ ይመስለኛል ተብሎ ይታረም። ዳዲ “ቢዚ” ነው ። አገልግሎት ይበዛበታል። ሳሎን በምትገኝ አንድ ጥግ ቦታ ላይ ትልቅ ኤአቴ የሰጠችን ጠረጴዛ  እና አንድ ወንበር እና ብዙ መፅሃፍት አለው ።መፅሃፍት ስላችሁ ታዲያ ሌላ መፅሃፍ እንዳይመስላችሁ። መፅሃፍ ቅዱስ ነው። አባቢ የሌለው የመጽሀፍ ቅዱስ አይነት መኖሩን እጠራጠራለሁ። ዳዲን እኔ ከማገኘው ይልቅ ጓደኞቹ ያገኙታል!አያስቅም? ። እኔ ስለሱ ከማውቀውም ይልቅ የቸርች ህፃናት ስለሱ የሚያውቁት ይበልጣል። ብዙ ወደ ቤት ከመጣ ልበሱን ቀይሮ ወደ ጥናት ስለሚሄድ እና  ስለማናወራ ይናፍቀኛል። ነገር ግን አንዳንዴ ደግሞ ያናድደኛል። ልክ እሱ ሲመጣ ቲቪ ይጠፋል። ከዚያ በ¹ላ ፀሎት ይጀመራል። ዳዲ ሲፀልይ ያሳዝናል። ነገር ረጅም ነው። ልክ እንደ ህንድ ፊልም!

አጭር፣ብዙ የማታወራ፣ሁሉ ነገሯ በመጠኑ የሆነች፣ስትሄድ ቦርሳዋን ብብቷ ውስጥ ጥብቅ አድርጋ የምትሄድ፣ረጅም ወደ ¹ላ የተጎነጎነ ፀጉሯ ላይ መሀል ለመሃል ሽበት ጣል ያደረገባት ሴት ካያች ያቺ ማሚ “ኬክ ነች”! ማሚ ስራ የላትም። እንደ ማሚ የሰው ስራ የማይጥመው ሰው አይቼ አላውቅም። እቤት ውስጥ ሰራተኛ ብትኖርም እንኳን ስራውን በሙሉ የምትሰራው ግን ማሚ  ነች። ማሚ ሰው በጣም ነው የምትወደው። ሰው ሁሉ ልክ እንደኛ “ማሚ” እያለ ነው የሚጠራት። ማሚን የማይወዳት ታናሽ ወንድሜ ቤቢ ብቻ ነው። ለምን  እንደሆነ ታውቃላችሁ? “ፀሎት ታስረዝማለች” ይላል።  ዳዲ በሌለ ጊዜ እቅፍ አድርጋ ጭኗ ላይ ታስተኛኝ እና ትዘምርልኛለች ፣ትፀልይልኛለች፣በልጅነቷ ስላጋጠሟት የሚያስቁ ነገሮች እየነገረች ታስቀኛለች። አንዳንዴ ግን ከዳዲ በበለጠ ታናድደኛለች። እኔና ቤቢ የሆነ ነገር   ማድረግ ስንፈልግ የተለያየ ሰበብ ትፈጥራለች።

1)     እግዚአብሄር ደስ አይለውም !( “ቤቢ ይሄ እግዚአብሄር ደስ የሚለው ነገር ምንድን ነው ይላታል?”)

2)    አባታችሁ ይቆጣል !(ቤቢ እጁን እያወናጨፈ“መቼ ነው ሳይቆጣ የቀረው?” ብሎ ይመልስላታል)

3)    ሰው ምን ይላል! (ቤቢ ደግሞ “ሰው ምን አገባው?” ይላታል እጁን ከላይ ወደ ታች እያወናጨፈ።)

4)    እናንተ እኮ የፓሰተር አማረ ልጆች ናችሁ እንደፈለጋችሁ መኖር አትችሉም! ( ቤቢ ሆዬ “ማን ውለዱኝ አላችሁ?”ይላትና እርፍ )

ታዲያ አታበሽቅም? ግን ብትቀርቧት ነፍስ ናት ። ማለት ሰው ትረዳለች። እግዚአብሄር የማያስከፋ እስካልሆነ ድረስ አንዳንድ ነገር እንድናደርግ ትፈቅዳለች። እኔ ፊልም እንዳይ ቤቢ ደግሞ እግር ኳስ እንዲያይ ትፈቅዳለች። ማሚም ሆነ ዳዲ ለድርድር የማያቀርቡት ነገር ፀሎት ነው። እኔ “ዳዲን ስለምፈራ” “ማሚን ላለማሳዘን እፀልያለሁ” ቤቢ ግን  አልነግራችሁም!

ቤቢሹ የአራት ዓመት ታናሽ ወንድሜ ነው። የፊታችን ህዳር አስራ ሶስት አመቱን ይይዛል። ኳስ ነፍሱ ነው። የማንችስተር ደጋፊ ነው። ለሻምፒዮንስ ሊግ ማንችስተር የተሸነፈ ጊዜ  ምግብ አልበላም ብሎ ዳዲ ሲቆጣው ነው የበላው። ቤቢ ኳስ ሲጫወት ውሎ ልክ ዳዲ ሊገባ ሲል አቧራ መስሎ ነው ወደ ቤት የሚገባው። ጓደኞቹ ትምህርት ቤት እንደሚደባደብ ይነግሩኛል። አንዳንዴ ፊቱ እሰኩየር ሉክ መስሎ ይመጣል። ማሚ በየግዜው በአስተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ብትጠራም ለዳዲ ግን አንድ ቀንም ተናግራ አታውቀውም። ማሚዬ እኮ ታሳዝናለች ። አንድ ቀን በሌሊት ተነስታ እኔን በተኛሁበት መጥታ ፀልያልኝ ስትሄድ ሰማ¹ት እና ወደ ቤቢ ክፍል ስትገባ ቀስ ብዬ ሳያት ያየሁትን ማመን አቃተኝ። ማሚ ከቤቢሹ አልጋ ጎን በጉልበቷ ተንበርክካ በግንባሯ መሬት ላይ ድፍት ብላ ታለቅሳለች። ልብሱን ታቅፋለች፣ወደ ሰማይ ታንጋጥጣለች፣በዝቅተኛ ድምፅ ስትንሰቀሰቅ ይሰማል።ሰውነቴ ከራስ ፀጉሬ እሰከ እገርጥፍሬ ተንቀጠቀጠ በደን እገሮቼን እጎተትኩ ተጠግቼ ተጠመጠምኩባት።እያለቀስኩ እምባዋን በመዳፌ እጠርጋለሁ እሷም የኔን ትጠርጋለች…ለረጅም ጊዜ ተላቀስን…ቤቢ ግን ነፍሱን ስቶ አንኮራፋል አልፎ አለፎ በቅዠት “አቀብለኝ…አቀብለኝ …ቹቼ…አቤክስ..” ይላል። ግን እናቶች ሁሉ እንደሷ ይሆኑ ? አባቶች ሁሉ ደግሞ ልክ እንደ ዳዲ ቢዚ ይሆኑ? ልጆች በሙሉ እንደ ቤቢ አስቸጋሪ ይሆኑ?

Advertisements

ምን ሐሳብ አለዎት?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s