Uncategorized

የሐዊ ማሰታወሻዎች (ረጅም ልብወለድ)

ምዕራፍ አንድ

ክፍል አንድ

ከዕለታት አንድ ቀን

መስኮቱ ላይ የሚያርፈው የማለዳ ፀሃይ በወርቃማው መጋረጃ ላይ ሲያርፍ ቤቱ ውስጥ የሚገኙ ነገሮችን በሙሉ ወርቃማ አስመስሏቸዋል። ወርቃማ አልጋ፣ወርቃማ የቀርክሃ ወንበር ፣በየቦታው የተዝረከረኩ ወርቃማ ካልሲዎች ፣ወርቃማ ነጠላ ጫማ፣ ወርቅማ ኮመዲኖ ላይ የተቀመጠ ወርቃማ የእጅ ቦርሳ፣ ከወርቅማው የአልጋ ልብስ ሹልክ ብሎ የወጣ  ክብ ወርቅማ ፊት የሚያማምሩ ግን የተከደኑ ወርቅማ አይኖች፣ ስልክክ ያለ ወርቅማ አፍንጫ፣የልብ ቅርፅ ያላቸው ወርቅማ ከናፍሮች እና ወርቃማ የፀጉር ዘለላዎች ከወርቃማው ሻሽ ሾልከው አልጋው ላይ ተበትነዋል።

በርቀት የታክሲዎች ድምፅ በታክሲ ረዳቶች “አራት ኪሎ አራት ኪሎ ፤ ማዞሪያ ብረትድልድይ” የሚል ድምፅ ታጅቦ በረቀት ይሰማል። በዚያች የክብሪት ቀፎ በምታክል ቤት ውስጥ በወፎች ጫጫታ የማን እንደሆነ በማይታወቅ መዝሙር ታጅቦ የሚሰማው ድምፅ የእሷ ለስለስ ያለ ትንፋሽ ብቻ ነው።ቤቱ በወርቃማው ብርሃን  ደምቆ የወርቅ ጉማጅ እንጂ መኖሪያ ቤት አይመስልም። ድንገት የእሷን ትንፋሽ ብቻ ሲያስተናግድ በነበረው ክፍል ውስጥ “ጭርርርርር….ዝዝዝ…” በሚል ድምፅ ደፈረሰ። ሃዊ አልጋዋ ውስጥ እንዳለች እጇን ሰድዳ ትንሽ ተንቀሳቃሽ ስልኳን ሆዷ አካባቢ በመዳበስ  ፀጥ አሰኘቻት። ከላይዋ ላይ የአልጋልብሱን አሽቀንጥራ ጥላ ከአልጋው ተስፈንጥራ ወጣች። ትናንሽ የሚያሳዝኑ እግሮቿን አሰቀያሚ ትልቅ ነጠላ ጫማ ውስጥ ሸጎጠቻቸው። ብርማ የሌሊት ልብሷ የጡቶቿን እምቡጥነት እና የዳሌዋን ስፋት በማሳየት ወጣትነቷን  ያሳብቃል ። ወርቃማዎቹን መጋረጃዎቹን ገልል አድርጋ መሶኮቱን ወለል አድርጋ ከፈተችው። ከውጭ የተንደረደረው ደራሽ የብርሃን ጎርፍ ቤቱን ሲያጥለቀልቀው አይኖቿን በትናንሽ እጆቿ አሻሽታ እጆቿን ወደ ኮርኒሱ ቀስራ ራስ ቅሏን ወደ ¹ላ  አዘንብላ አፏን ገርበብ አድርጋ ተንጠራራች ።ድንገት ጭንቅላቷ ጠርዝ ላይ ይገኝ የነበረው  ሰማያዊ ሻሽ ሲወድቅ ጥቁር ረጅም ፀጉራ ትከሻዋ ላይ ፈሰሰ። አልጋው ጠርዝ ላይ ተመልሳ ተቀመጠች። ውስጥን ሰርስረው የሚያዩ የሚመስሉ ቡናማ አይኖቿን  ቦዘዝ አድርጋ በመሰኮት በኩል አርቃ ወረወረቻቸው።

እርስ በእርሱ ተቆጣጥሮ አናቱ ላይ የኣጋዘን ቀንድ የሚመስል ፀጉር ያለው፤ፊቱ ክብ እና ፈርጠም ያለ፣ከላይ ሰልከክ ብሎ ጫፍ ላይ ሲደርስ የሚሰፋ አፍንጫ ያለው፤ ከናፍሮቹ አጠቋቆራቸው የክሰል ምድጃ የሚመስሉ፤ ከአንገቱ ላይ አደፍ ያለች የአንገት ልብስ  የሚጠመጥም ፤አብረውት የተፈጠሩ የሚመስሉ ቡኒ የቆዳ ጃኬት እና ጥቁር ጅንስ ሱሪ የሚያዘወትር የትምህርት ቤት ጓደኛዋ ትዝ አላት።ዐነደ ምሽት ጀንበር ሊጠልቁ የተቃረቡ  አይኖቹን  እያስለመለመ ፣ጫፋቸው በእሳት የተለበለበ በሚመስሉ ጣቶቹ ፊቱን እያሻሸ“ፕሊስ ጀስት ዱ ኢት… ለእኔ ስትይ?… ምን መሰለሽ እንድንወያይበት እኮ ነው?” ዘርዘር ያሉ ጥርሶቹን ብልጭ አደረገላት።

ቤዛ በትምህርት ቤታቸው ሚኒ ሚዲያ የተጨበጨበለት ጋዜጠኛ ነው። ድምፁን የሚወዱ ተማሪዎች አለምነህ ዋሴን ፤ ቀልዱን የሰሙ ደግሞ ሰይፉ ፋንታሁንን እንደሚተካ አይጠራጠሩም። ታዋቂ ከሆነባቸው ፕሮግራሞቹ መካከል “ወጣነት” በሚል ርዕስ ረቡዕ በዕረፍት ሰዓት የሚያቀርባቸው መጣጥፎች ናቸው። ለዚህ ፕሮግራም የሚሆን ፅሁፍ ለማዘጋጀት የሃዊን የዕለት ከዕለት ህይወት እንደማሳያ ለመጠቀም አስቧል። ጥሩ ልጅ ነው። ሃዊ በተለይ የምትወድለት ነገር አላት። ስለሰው ክፉ ማውራት አይወድም። በጣም ከባድ ነገር  ሲደርስበት እንደተለመደው ፊቱን በውስጥ እጁ እያሻሻ “ህይወት በኳልኩሌሽን አትመራም ልጅት” ይላታል ሳቅ ብሎ።

ኮመዲኖ ላይ ያለውን ቤዛ የሰጣትን ትልቅ ባለ ሰባ ሁለት ገፅ ‘ራይቲንግ ፓድ’ ተመለከተች እና ደከማት። “ይሄን ሁሉ ልፅፍ?” ስትል ራሷን ጠየቀች እና በድካም ስሜት ፈገግ አለች። ወዲያው ደግሞ የቤዛ ቁምነገረኝነት ፤ክርስቲያን መሆኗን ስለሚያውቅ እንዳይሰናከልባት፤ደግሞም ከፃፈችው በ¹ላ ስታነበው  ደስ የሚል መሆኑን  ለራሷ ነግራ እራሷን አሳመነች። ትልቁን ማስታወሻ ከኮመዲኖው ላይ አነሳችና እና አልጋው ላይ ወጥታ ግድግዳውን ተደገፈች እግሮቿን አጠላልፋ ፤ረጅም ፀጉሯን እየጎነጎነች፣ አይኖቿን የማስታወሻ ደብተሩ የመጀመሪያ ገፅ ላይ ተከላ ከናፈሮቿን ሞጥሞጥ አድርጋ ስለምትጽፈው ነገር አሰበች። ድንገት የሃሳብ ጎርፍ ወደ አዕምሮዋ ነጎደ። ሀሳቦች በፊደላት ጉያ እየጋለቡ ወደሷ ሲገሰግሱ ቃል ሃረግ ፣ሃረግ አረፍተ ነገር፣አረፍተ ነገር አንቀፅ፣አንቀፅ ምዕራፍ አየሆኑ ሲከመሩ በእዚነ ህሊናዋ ታያት። ነገርግን እንዴት መጀመር እንደሚኖርባት ስታስብ ጉልበት ሲከዳት ታወቃት። ፈጠን ብላ ከማስታወሻው ውስጥ እሰኪብርቶ አወጥታ ባዶ ገፅ ላይ “የሃዊ ማስታወሻዎች” ስትል በትልቁ ፃፈች። አንድ ገፅ ገልብጣም  ፊደላትን ቃላት፣ ቃላትን ሃረግ፣ ሀረጋትን አረፍተነገር፣ እያደረገች ማሰለፉን እንዲህ ስትል ጀመረች።

ይቀጥላል…..

Advertisements

2 thoughts on “የሐዊ ማሰታወሻዎች (ረጅም ልብወለድ)

ምን ሐሳብ አለዎት?

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s